ወቅታዊ ጉዳዮች

የጌዴኦ አርሶ አደሮች የትግል ውሎ

የጌዴኦ አርሶ አደሮች የትግል ውሎ፣

           / መሬት ‘‘ ያኣ ’’ ነው/

 

በደቡብ  ብሄሮች ፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች  የነፍጠኛውን ስርዓት በመታገል ጉልህ አስተዋጽዖዎች አበርክተዋል። ከእነዚህ የክልሉ የብሄር ብሄረሰብ ትግሎች መካከል የጌዴኦ ብሄረሰብ ትግል በአብነት ይጠቀሳል። የጌዴኦ ህዝብ የነፍጠኛውን ስርዓት የተቃወመባቸው መሠረታዊ ምክንያቶች ምንድን ናቸው?

 

የጌዴኦ ህዝብ የነፍጠኛው ስርዓት ወደርሱ ከመምጣቱ በፊት የራሱ በሆነ ፖለቲካዊ ፣ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ  አስተዳደር ይመራ ነበር፡፡ የህዝቡ ፖለቲካዊ ፣ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ  አስተዳደር በመሬት ጉዳይ ላይ የሚከተላቸው የመሬት ስሪት ስርዓቶች ነበሩት፡፡

 

በጌዴኦ ፖለቲካዊ ፣ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ አስተዳደር መሠረት የመሬት ባለቤት “ያኣ” /ጠቅላላው የጌዴኦ ህዝብ ነው/ የ “ያኣ” /ህዝብ/ ንብረት የሆነውን መሬት፣ ይህንን ንብረት በተገቢው መንገድ እንዲያስተዳድሩ በተመረጡ ሰዎች አማካኝነት ተሸንሽኖ ለደራባ /ለእየጐሣው/ ይሰጣል። ደራባም ከ “ያኣ” የተቀበለውን መሬት በጐሣው ውስጥ ለሚገኙ ቤተሰቦች ፍትሀዊ በሆነ መንገድ ያካፍላል። መሬት ለማከፋፈል የተሰጣቸውን የህዝብ አደራ ደራባዎች በተገቢው መንገድ መወጣትና አለመወጣታቸውን የሚከታተል፣ ከእያንዳንዱ ጐሣ ተውጣጥቶ የተሰየመ የመሬት አስተዳደር ጉባኤ አለ።

 

የ“ያኣ” መሬት ለህዝብ ከተከፋፈለ በኋላ የሚፈጠር አዲስ ቤተሰብ ሊኖር ይችላል። ይህ ቤተሰብ እንዴት በፍትሀዊነት ተስተናገደ? እንዴትስ ያስተናግድ ነበር? የሚል ጥያቄ ሊከተል ይችላል።

 

አዲስ የተመሠረተ ቤተሰብ ሲኖር ሙሽሪት ከባልዋ እናት መሬት ተቆርሶ እንዲሰጣት ይደረጋል፡፡

የመሬት ስጦታው ጋብቻውን ለማፅደቅ ብቻ የሚቀርብ አይደለም። ተጋቢዎች በዚህ መሬት ላይ ያላቸው የህይወት ክህሎት ጭምር ተፈትኖ የማያልፍበት ነው። በዚህ በተሰጠው መሬት ላይ የምርት ክህሎቱን በሚገባ ያልገለጠው አዲስ ቤተሰብ ከ“ያኣ” ተጨማሪ መሬት መጠየቅ አይችልም።

 

ተጨማሪ መሬት ሲፈልግ ግን ለቤተሰቡ ታላቅ በሆነ ሰው አማካኝነት ጥያቄውን ለጐሣው የመሬት አስተዳደር ጉባኤ ያቀርባል። ጉባኤው ጥያቄውን ተቀብሎ ለ”ያኣ“ ያስተላልፋል። ‘‘ያአ’’ መሬት ጠያቂው ቤተሰብ መሬቱን ለመጠቀም ብቻ ሳይሆን መሬቱን ለመጠቀም ያለውን አቅም ፈትኖ፣ ጠያቂው ለህብረተሰቡ ያበረከተውን አስተዋፅዖ ጭምር መዝኖ÷ ይሰጠው የሚል ውሳኔ ሲያስተላልፍ “ሙር” የሚባሉ መልዕክተኞች፣ መሬት አካላዮች ተልከው መሬቱን ያካልላሉ።

 

‘‘በጌዴኦፖለቲካዊ ፣ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ስርዓት ህዝብ ያልሰፈረበት መሬት መጠባበቂያ ሆኖ ይቀመጣል እንጂ ማንም በርስትነት አይዘውም። መሬቱ ለእርሻ ተግባር እንዲውል ካስፈለገም ለህዝብ የማከፋፈል ስልጣን የነበራቸው አባገዳውና ሥርዓቶቹ ነበሩ። የመሬት ክፍፍል በሚያስፈልግበት ወቅት ህዝቡ ተሰብስቦ ስለ አከፋፈሉ ተመካክሮ ይወሰናል። ክፍፍሉም በተቻለ መጠን ፍትሀዊ ነበር። ብዙ ቤተሰብ ያለው በለጥ ያለ መሬት ያገኛል። በተረፈ መሬት የሚከፋፈለው በእኩልነት ነበር። ለም ያልሆነ መሬት የደረሰው ወይም መሬት የነሰው ወገን ይግባኝ የመጠየቅ መብቱም የተጠበቀ ነበር። አንድ ሰው መሬት ከተሰጠው በኋላ ከይዞታው የሚነቅለው ምንም ኃይል አልነበረም ’’

 

ቤተሰብ በዚህ መልኩ የተሰጠውን መሬት ለልጆች ማውረስ እንጂ መሸጥ መለወጥ አይችልም።

ይሁንና ከዚህ የጌዲኦ የመሬት ስሪት ስርዓት ጋር ፍፁም ተቃራኒ የሆነ የመሬት ስሪት የነፍጠኛው ስርዓት ይዞ ወደ ጌዴኦ ምድር መጣ። የመሬት ባለቤት የሆነውን ህዝብ በአዲስ አይነት የመሬት ስሪት ለማስገበር ወደ ደቡብ የመጣው ነፍጠኛ ከስድስት መቶ ሺህ እስከ ስምንት መቶ ሺህ የሚገመት እንደነበር መረጃዎች ይጠቁማሉ። ወደ ጌዴኦ አውራጃ ብቻ ከሶስት እስከ አራት ሺህ የሚቆጠር ነፍጠኛ ሰፋሪ መጥቶ ነበር።

በሰፋሪነት ለመጣው ለዚህ ነፍጠኛ መተዳደሪያ መፍጠር አስፈላጊ ነበር። በመሆኑም ያልለሙ የተባሉት መሬቶች ላይ ቀላድ ተጣለባቸው። ለመጤዎችም ተከፋፈሉ። ገሚሱ በማደሪያነት፣ ከፊሉ በምሪትነት÷ የቀረው በሽያጭ ለመጤዎቹ ተሸንሽኖ ተሰጠ። የመሬቱ አብዛኛው ዕጅ የመንግስት መሬት ነው ተብሎም ለወታደሮች ታደለ። የቀረውም መሬት በአነስተኛ ዋጋ ተቸበቸበ። ይህ ድርጊት የጌዴኦን ህዝብ አሳዘነው።

 

የጌዴኦ ህዝብ በነፍጠኛው ስርዓት ተቀርፀው ከመጡት የመሬት ስሪት ስርዓቶች መሬት የገበሬው ንብረት ሆኖ ግብር የሚከፈልበትን አሠራር አልተቃወመም። ተቃውሞው ከሌሎቹ ስሪቶች ጋር ነበር። ምክንያቱም የተቀሩት የመሬት ስሪቶች፣ ጭሰኛው የባላባቱን መሬት ተገዶ የሚያርስበት፣ ሣር አጭዶ የባላባቱን ከብቶች የሚቀልብበት፣ ያመረተውን ምርት ከየዓይነቱ ለባለርስቱ የሚገብርበት፣ እርቦ የሚሰፍርበት፣ የቡና ማሳው ተገምቶ የተገመተውን ግብር ለፊውዳሉ ለመስጠት እንኳ ለገማቹ የጤዛ ተብሎ ክፍያ የሚጠየቅበት፣ አውድማ የሚያዘጋጅበት፣ የፊውዳሉን አጥር የሚያጥርበት፣ የራሱን እንጨት ፈልጦ የሚያስረክብበት በመሆኑ ነው - መቃወሙ፡፡ ልጆቹ የባለርስቱን በግ የሚያግዱበት፣ የጭሰኛው ሚስቶች ተራ ገብተው ለፊውዳሉ ቤት አዛባ የሚዝቁበት፣ የሚፈጩበት፣ የሚጋግሩበት፣ አስፈጊውን የጉልበት ስራ እንዲያከናውኑ የሚገደዱበት ሁኔታ በመኖሩ ነበር ተቃውሞ የተነሳው።

 

ይህ የተቃውሞ ጭቅጭቅና ሙግት “ሀ” ብሎ የተጀመረው በአፄ ሚኒልክ ዘመነ መንግስት ነው፡፡ በወቅቱ ባልቻ አባ ነፍሶ ወደ ጌዴኦ መጥተው ይህንኑ የመሬት ስሪት ስርዓት በህዝቡ ላይ ጭነው ነበርና። እናም ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ተቃውሞ እና ጭቅጭቁ ሳይቋረጥ ቀጠለ። ያኔም ተቃውሞና ጭቅጭቁ ለማዕከላዊ መንግስቱ የቀረበ ቢሆንም መፍትሔ አጥቶ ዘለቀ። ጥያቄው ጥያቄ ብቻ ሆኖ ዕልባት ሳያገኝ ቀረ።

 

ጥያቄው ዕልባት ሳያገኝ እንደተንጠለጠለ÷ ህዝቡ የገዛ መሬቱ ላይ ሌላ ኃይል መጥቶ፣ በገዛ የመሬት ስሪት ስርዓቱ ላይ ሌላ ጨቋኝ ተቀምጦበት ኢፍትሀዊ የመሬት ስሪት ስርዓት ተጭኖበት የጭለማ ዘመናትን አሳልፏል።

 

በዚህም ባልቻ አባነፍሶ የጌዴኦን ባህላዊውን የመሬት ስሪት ስርዓት ሽረው የነፍጠኛው የመሬት ስሪት ስርዓት በህዝቡ ላይ ከጫኑበት ዘመን ጀምሮ እስከ አፄ ኃይለስላሴ የአገዛዝ ዘመን ማብቂያ ድረስ ብሄረሰቡ የጭቆና ጊዜያትን ሲገፋ ቆይቷል። ይሁንና ሁሌም እምቢተኝነቱን እንደገለፀ፣ ብሄራዊና መደባዊ ጭቆናዎቹ እንዲወገዱለት እየተከራከረ ነበር። መከራከርና አቤቱታው ያመጡለት አንዳች ፋይዳ ግን አልነበረም። ጨቋኙም አቤቱታ ሰሚውም ያንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች ስለነበሩ ትርጉም አልነበራቸውም፡፡

 

በአፄ ኃይለስላሴ የአገዛዝ ዘመንም ስርዓቱ አልተለወጠም። ቀደም ሲል የነበረው ስሪት እንዳለ ሆኖ ለሠራተኛው፣ ለፖሊሲና ለጦር ሰራዊት መኮንኖች እንዲሁም ለባለርስቶች መታደሉ ቀጠለ።

የጌዴኦ አካባቢ መሬት በጣም ለም ከመሆኑ የተነሳ በየጊዜው ቀላድ ይጣልበት ጀመር። አርሶአደሩ ቀስበቀስ መሬቱን እየተነጠቀ የመጤዎች አሽከር የሚሆንበት ሁኔታ ይበልጥ ተስፋፋ። ብዝበዛው ተጧጧፈ። የአርሶአደሮቹ ስቃይ በረታ። የጌዴኦ ጭሰኛ ገበሬ በራሱ መሣሪያ አርሶ ካመረተው ምርቱ አንድ አራተኛውን ለባለርስቱ መገበሩን ቀጠለ። ባለርስቱም በዲላና በሌሎች ወረዳ ከተሞች ተቀምጦ እየተሰፈረለት፤ ሳይሰራ የሰዎቹን ወዝና ላብ መጠጣት፣ መምጠጡ እየጣፈጠው ሄደ። ከከተማ መሬቱን ለመጐብኘት ሲመጣ የራት እየተባለ ለባለርስቱ ወደመጣበት እስኪመለስ የማብላትና የማጠጣት ሸክም ወድቆበታል።

 

ጥር 26 ቀን 1952 ዓመተ ምህረት  አንድ ጐጃ ጉራቻ የተባለ፣ ዳማ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የሚኖር አርሶአደር ቡና በደቦ እየተሰበሰበ ነበር፡፡ ከ70 የሚበልጡ አርሶአደሮች የዚህን አርሶአደር ቡና እየለቀሙ ሳለ በቀለ ገዳ የተባለ፣ መሬቱ የኔነው የሚል ፊውዳል ቡናው እየተለቀመ የመሆኑ ወሬ ደርሶት ልጆቹን እና በየአካባቢው ያሉትን ፊውዳሎች አሰባስቦ ወደ ስፍራው ገስግሶ መጣ፡፡ ወደ ስፍራው ከንጋቱ 12 ሰዓት ላይ ከአስከተላቸው ጋር ደረሰ። ሳይገመት ለምን መሰብሰብ እንደጀመሩ አርሷደሮቹን ሲጠይቃቸው ከአርሶደሮቹ መካከል አንድ ገበየሁ የተባለ አርሶደር ለአያሌ ዘመናት ጉልበታችንና ምርቶቻችን በዝብዛችሁናል፤ ከእንግዲህ ይበቃችኋል፤ ጉልበታችንንም መሬታችንንም ከዚህ በኋላ ለማንም አናካፍልም ሲል አምርሮ ተናገረ።

 

አንድ ፊውዳል የገበየሁን ግንባር ሽጉጥ ተኩሶ መታው። ገደለው። ኡኡታ ተነሣ። ጩኸቱ ከተራራ ተራራ አስተጋባ። በምችሌ እና ዳማ መካከል የቺቹ ወንዝ የሚያልፍበት ሸጥ አለ። ጩኸቱ ወንዟ የምታቋርጠውን ሸጥ ዘሎ ሚችሌ ድረስ ተሰማ።  

 

ከሚችሌ አርሶአደሮች ጠመንጃዎቻቸውንና ጦሮቻቸውን ይዘው ወደ ዳማ ጐረፉ። በሀይቻዎች ትዕዛዝ መሠረት ገዳዮቹን ፊውዳሎች አርሶአደሮቹ ከበው ያዙ። በወቅቱ የነበረውን ሁኔታ ሀጌ እንዲህ ያስታውሳሉ፡-

 

‘‘ህዝቡ ገዳዮቹን ከቦ አደረ። ዕለቱ አርብ ነው። ህዝቡ እንደ ትናንት በደቦ ቡና ለቀማ ላይ ነበር። አልበላም፤ አልጠጣም። ሳይበላ ሳይጠጣ እዛው ገዳዮቹን እንደከበበ አደረ። ህዝቡ አስክሬኑን ለአቤቱታ ይዘን እንሄዳለንም ሲል ጠየቀ። የመጣው ጦር ይዛችሁ አትሄዱም እዚሁ ቅበሩ አለ። አንቀብርም÷ ትቀበራላችሁ ጭቅጭቅ ተፈጠረ።

 

“ህዝቡ ስላልበላ- ስላልጠጣ እዚያው ከቦ እንደተቀመጠ ሴቶች ስንቅ አመጡ። ስንቁ መጥቶ እየተመገብን ሻምበል ዘርጋው የሚባል ሰው ሰራዊት መርቶ መጣ። ይዞት የመጣው ጦር ሰራዊት የሚመገበውን ህዝብ ራቅ ራቅ ብሎ ከቧል። እየበላን እያለ ድንገት፣ እንደተቀመጥን ተኩስ ተከፈተብን። 60 አርሶአደሮች እዚያው አለቁ። ሴት ወንድ አልለየም። የተቀረው ነፍሱን ይዞ፣ ሸሽቶ አመለጠ። ህዝቡ በረገገ፤ ቤቱ መቃጠል ጀመረ። ዘረፋው ቀጠለ። በየቦታው የተኩስ ድምጽ ብቻ ሆነ።

“ከሚችሌ የተነሱትና ጩኸቱን ሰምተው ወደ ዳማ ከተሻገሩት፣ ነፍሰ ገዳዮቹን ፊውዳሎች ከበው ካደሩት አርሶአደሮች መካከል ፣ የሞተው ሞቶ ከሞት የተረፈው ሸሽቶ ወደሚቻሌ ሲመጣ ቤቱ ተቃጥሏል፡፡ ቡናው ተቃጥሏል፡፡ ንብረቱ ተዘርፏል…’’

 

ግጭቱ እየተባባሰ፣ አመፁ እየተስፋፋ ነው። ምሬቱ ገንፍሎ ወጥቷል። ይህንን የገነፈለ የአርሶአደር መሬት በኃይል ለማብረድ ከታች ከሚችሌ ሲሰታ አቅጣጫ÷ በወናጐ በኩል እንዲሁም ዳማ ላይ ብጥብጡ በተነሳበት አካባቢ ባሉ አቅጣጫዎች የፊውዳሉ ጦር አርሶአደሩን በጥይት ገሎ፣ ያልገደለውንም ገርፎ ተገዥ ለማድረግ ኃይሉን አዘመተ።

 

 

ይሁንና ይህ የተጋጋለ አመፅ ወደፊት ሊቀጥል አልቻለም። መንግስት ከፊውዳሎች ጐን ቆመ። አልፎ አልፎ የነበሩት ተተኳሽ የጦር መሣሪያዎችም በቂ ጥይት አልነበራቸውም። ቁጥራቸውም ጥቂት ነበር። ቀለብም በበቂ ሁኔታ አልነበረም። የጦር መሣሪያ እንዳያስገባና ቀለብ እንዳያገኝ ፊውዳሎቹ አርሶአደሩን በሚገባ ተቆጣጠሩት።

 

በዚህም የጌዴኦ ህዝብ በጦርነቱ በእጅጉ ተጉዳ። ከወገኖቹ 200 ያህል ሰዎች ተገደሉበት። የወደመበት ንብረትም ከ1 ሚሊየን ብር በላይ ነበር።

 

ከጦርነቱ በኋላ ሀይቻዎች እንደጥፋተኛ ተቆጥረው ቅጣት ተጣለባቸው። በነፍስ ወከፍ 500 ብር ቅጣት ሲጣልባቸው ቅጣቱን ለመክፈል ሲሉ መሬታቸውን ሸጡ። የገዟቸው ጦርነት የገጠሟቸው ፊውዳሎች ናቸው። ሐይቻዎቹ እጅግ በጣም ደሀ ከመሆናቸው የተነሳም ከርስታቸው ተፈናቅለው ጀምጀምና አሬሮ ወደተባሉ አካባቢዎች ተሰደው ለመኖር ተገደዱ።

 

የጌዴኦ አርሶአደሮች አመፅ የፊውዳሉን ስርዓት አሽቀንጥሮ ለመጣል ለተደረጉት የኋላ ፀረ ነፍጠኛ ትግሎች አስተዋጽዖ ነበረው። ህዝብ ከተደራጀ ስርዓቱን በኃይል ፈንቅሎ መጣል እንደሚችል በቂ ምልክት የሰጠ ነበር። በኋላም ይኸው ተፈፃሚ ሆኗል። በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ በብሄራዊና መደባዊ ጭቆናዎችን ያደርስ የነበረው ስርዓት ከስሩ ተመነገለ። መሬት ላራሹ ሲታወጅ የጌዴኦ ህዝብ ወደ ርስቱ ተመለስ። የተቀማውን መሬቱን መልሶ አገኘ።

 

ምንጭ ፦ -የጌዴኦ የሀገር ሽማግሌዎች

     - የጌዴኦ ብሄር ታሪክ 2000 ዓም

    -ተራሮችን ያንቀጠቀጠ ትውልድ ቅጽ 3