የስምጥ ሸለቆ ታጋዮች የትግል ጉዞ

የስምጥ ሸለቆ ታጋዮች የትግል ጉዞ

 

አልተዘመረላቸውም፣ አልተፃፈላቸውም፣ ታሪኮቻቸውን ግርዶሽ ከልሎታል። እነዚህ ያልተዘመረላቸው፣ ያልተነገረላቸው አናብስት ዛሬም ይዘምራሉ። ከሁለት አስርተ ዓመታት በላይ ያስቆጠረው ተጋድሏቸው ትዘታ ህሊናቸው ውስጥ በማይለቅ ቀለም ተጽፏል። ሞት እንጂ ይህንን የታሪክ ደማቅ ቀለም ከህሊናቸው የሚደመሰስ ኃይል በምድር ላይ የሚኖር አይመስልም። ያልተዘመረላቸው ቢሆኑም እነሱ ግን ያን ጊዜ ለነፃነት የዘመሩትን መዝሙር አሁንም ይወጡታል - በዜማ። ዜማዎቻቸው መንገደኛን ጭምር የሚያፈዙ፣ የዕንባ ከረጢቶቻችን የሚያፈነዱ ናቸው። ይዘምራሉ…

 

ከቀዬ ከትውልዴ መንደሬ ፣

የወጣሁት የኋሊት ታስሬ ፣

በደርጐች ተግባር ተለይቼሽ ፣

አልኖርም ሁሌም እንደራቅኩሽ …

ይላሉ።

ይዘምራሉ እንዲህ እያሉ፡-

ኢትዮጵያ ለምለሟ ሀገሬ፣

ብረካም ካንቺ መፈጠሬ፣

ፋሺስቱ ወንድሞቼን በልቶ ፣

ተሰምቶኛል ዛሬ ግፉ በዝቶ…

ይላሉ፤የከለላቸው ግርዶሽ እንዲገፈፍ ይዘምራሉ…

በደርጐች የተረሸናችሁ፣

ለእውነት የተማገዳችሁ፣

አይቀርም ደማችሁ ፈሶ፣

ይበቀላል ኢህአዴግ ደርሶ …

ይላሉ።

ይዘምራሉ እንዲህ እያሉ፡-

ይሰማኛል ያለፈው ህይወቴ፣

የስቀይ ስብስብ ብሶቴ፣

ለደርጐች ዕድሜ መስዋዕቴ፣

ያበቃል ከእንግዲህ ልፋቴ።

ይዘምራሉ፤ ይዘምራሉ፤ የዘምራሉ።

 

ይህንን የትግል መዝሙር የፃፉት ታጋይ ተፈራ መስቀሌ ናቸው። ሃያና ሰላሣ ዓመታት ከተሸኙ በኋላ በሀልዮ የተቀመጠውን ይህን መዝሙር ሲነበብ ከጓዶቻቸው ጋር አብረው ከሚዘምሩት መካከል ደግሞ ታጋይ ደጉ ጥኢጦ አንዱ ናቸው። የእኚህን ታጋይ ያለፈ የትግል ታሪክ ስትሰሙ ደጉ በወጣትነት የትግል ዘመኑ ምን ዓይነት ጀግና ሰው እንደነበር ወለል ብሎ ይታያችኋል። ነበልባል ነው - ላንቃው እስከጠላቱ ድረስ የሚጥመለመል። ጀግና ነው -ጀግንነቱ አድማስ ጥግ ድረስ የተዘረጋ። ሞገድ ነው - ጠላቱን ጠራርጐ የሚነጉድ፡፡ ማዕበል ነው - የጠላቱን መንደር ንጦ የሚያናጋ። ይሁን እንጂ አልተዘመረለትም፣ አልተነገረለትም።

ደጉ የሀዲያ ተወላጅ ነው። በወጣትነት ጊዜው ከሀዲያ ወጥቶ አሰላ አካባቢ የመኖር ዕድል አጋጥሞታል። እዚያም በፖሊስ ስራዊት ውስጥ ተቀጥሮ ነበር። አሠላ አካባቢ በሚገኘው ፈጥኖ ደራሽ ፖሊሰ ካምፕ ውስጥ ነበር ኑሮው።

ታጋይ ደጉ፡-

“ጊዜው ወጣቶች ለዕድገት በሀብረት ዘመቻ የተሰለፉበት ነበር፡፡ በዘመቻው ላይ የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች የተሰለፉ ሲሆን የፖሊስ ሰራዊቱም ዘመቻውን የማስተባበር ስራ ይሠራ ነበር፡፡ በዚህ ምክንያት ዘዋይ ዱግዳ ወደሚባለው አካባቢ ተመድቤ መጣሁ።

“እዚያ ነው ለማ ከተባለው፣ ለመመረቅ አንድ ዓመት ከቀረው የዩኒቨርስቲ ተማሪ ጋር የተገናኘሁት። ለማ ጓደኛው አደረገኝ። አብሮኝ ነበር የሚተኛው። በሚስጥር ስለዲሞክራሲ አቅጣጫ፣ ስለ ስርዓቱ አስከፊነት ያስጠናኝ ጀመር። ወጣት ነህ ፤ጥሩ ጭንቅላትም አለህ፤ ለምን ከበሰበሰው ስርዓት ጋር አብረህ ትራመዳለህ አለኝ። ተማሪው የጠየቀኝ ጥየቄ የማመዛዘን ጥያቄ ስለነበር ልቤ የሱን ሀሳብ ወደ መከተል አዘነበለ። ውስጥ ውስጡን የተማሪዎች የንቅናቄ ሀሳብ ደጋፊ ሆንኩ. . .”

ከዚህ በኋላ ደርጐች ኢሀፓዎች የሆኑ ወጣት የፖሊስ ሠራዊቱ አባላት አሉ የሚል ድምዳሜ ላይ ደረሱ። በኢሀፓነት በተጠረጠሩት ወጣት የፖሊስ ሰራዊት አባላት ላይ እንደሚደረገው ሁሉ በደጉም ላይ ክትትሉ በረታ። ተከታትለው ወደ እስር ቤት ጣሉት።

አሠላ ፖሊስ መምሪያ ታሰረ። ወቅቱ ወጣቶች በፈላ ዘይት እግሮቻቸውን የሚጠበሱበት፣ በአለንጋ ስጋቸው እስኪነሳ የሚገረፉበት፣ ብልታቸው ላይ ድንጋይ ተንጠልጥሎ በስቃይ ብዛት የሰሩትንም ያልሰሩትንም እንዲለፈልፉ የሚደረግበት፣ የመከራ ሸክም ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ በወጣት ኢትዮጵያውያን ላይ የተከመረበት ነበር።

ደጉም ይህንን ያውቃል። መውጫ ቀዳዳ እንደሌለው ተረድቷል። ስጋንና ነፍስን ይዞ ከዛ እስር ቤት ውስጥ መውጣት አይቻልም። የሚቻል ነገር ግን አለ። ነፍስ ሰጥቶ በበድን፣ በቆሰለ ስጋ መውጣት።

ግርፋቱ ወደ እርሱ ቀረበ። ከዚሀ በፊት የማያውቀው የፖሊስ አባል መጥቶ ይገርፈው ጀመር። እየገረፈው፡-

“ኢህአፓ ነህ?” ይጠይቀዋል፡፡

“አይደለሁም!” ይመልሳል፡፡

“እጩ ነህ”

“አይደለሁም”

“ታሳቢ ነህ”

“አይደለሁም”

መቶ አለቃው እጁ እስኪዝል የገረፈው ቢሆንም በደጉ ላይ የሚፈፅመው ግርፋት ጠብ ያደረገለት አዲስ መረጃ ባለመኖሩ ፣ “ቆይ ዋጋህን ታገኛለህ አለና”፣ ትቶት ሄደ።

“ቆይ ዋጋህን ታገኛለህ!” የማለቱ ትርጉም ከደጉ የተሰወረ አልነበረም። በዚያን ጊዜ አልናገርም ያለ ዋጋው ሞት ነው። እናም እስር ቤት ውስጥ ሆኖ የመረሸኛውን ቀን ይጠብቅ ጀመር።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ሻውል ዘለቀ የሚባሉ የአሰላ አውራጃ ፖሊስ አዛዥ የሆኑ ሰው እስር ቤቱን ሲጐበኙ ደጉን አዩት፡፡ የልጆቻቸው ጓደኛ ሆኖ ያውቁታል። “ይህ ልጅ ምን አድርጐ ነው የታሰረው? ” ብለው ጠየቁ። ኢህአፓ ነው የሚል ምላሽ ተሰጣቸው። “ኸረ እባካችሁ ይህ ሊሆን አይችልም። ለማንኛውም እኔ ጋ አቅርቡት እስኪ” ብለው ትዕዛዝ ሰጡ። ተጠርጣሪው ኢህፓ፣ ደጉ እርሳቸው ዘንድ ቀረበ። “ከንባታ ጐበዝ ነው . . .” በወቅቱ ሃዲያም ከንባታ ተብሎ ነው የሚጠራው። እርሳቸውም “ከንባታ ጐበዝ ነው። ቅቤ ተቀብቶ ሰው ቤት ዘሎ ይገባል ሲባል አንተ ከኢሀፓ ጋር ትውላለህ?” ሲሉ ደጉን ጠየቁት።

“አልዋልኩም ጌታዬ! በእውነት አልዋልኩም. . .” ደጉ አለቀሰ። ለቅሶውን ባዩ ጊዜ አዛዡ ሆዳቸው ባባ። ከአካባቢው አርቀው ሊወስዱት፣ ከሞት መንጋ ሊያስመልጡት ፈለጉ።

“እሺ አሁን የት ትሄድ? ይኸው ሱማሌ መጥቶ ድሬደዋን አልፎ ወደ ናዝሬት እየተጠጋ ነው። እዚያ ብሰድህ ዛሬውኑ ትሞታለህ። ትንሽ እንኳን በህይወት ብትቆይ። በቃ ኤርትራ ትሄዳለህ . . .” አሉት፡፡

በነጋታው በማክ የወታደር መኪና ተሳፈረ። ኮልፌ ደረሰ። በሁለተኛው ቀን በቦይንግ 707 አውሮፕላን ተጭኖ ጉዞ ጀመረ። በዚያው ዕለት አስመራ ገባ። በዚያው ዕለት በሄሌኮፕተር ተጫነ። በዚያው ዕለት ናቅፋ ደረሰ።

ናቅፋ ላይ የተፋፋመ ውጊያ አለ። አንድ የደርግ ክፍለ ጦር በሻብዕያ ሠራዊት ተከቧል- ዙሪያውን፡፡ እናም ይህንን የተከበበ ሰራዊት ከመደምሰስ ለማስጣል ተብሎ የሰለጠነም ያልሰለጠነም ከኤሌኮፕተር ላይ በጆንያ ወደ መሬት ዝለል ይባላል፡፡ ደጉም ዘለህ ውረድ ተባለ። እኔ መዝለል አልተማርኩም፤ መዝለል አልችልም የሚል መላሽ ሰጠ፡፡ ዝለል አልዘልም ጭቅጭቅ ተፈጠረ። አልዘልም ግለደኝ! የደጉ የውሳኔ ሀሳብ ነበር።

ከኤለኮፕተሩ ላይ ወደ ነደደው የሳት ባህር ዘሎ ከመውረድ ይልቅ ሂለኮፕተር ላይ እያለ ሞቱን የመረጠው ደጉ፣ ምርጫው የሆነውን ሞት በመቀጣጫነት በሠራዊቱ ፊት እንዲቀበል ወደ አስመራ ተመለሰ። አስመራ መጥቶ ታሰረ።

ከታሰረ በኃላ ለግድያ ጦሩ ፊት በካቴና ታስሮ ቀረበ። ሞት ምርጫችን ነው በለን ብንወስንም በቀረበን ጊዜ ግን እንፈራለን። ምክንያቱም ከሰዎች ጋር ፍርሀት አለች። ከሰዎች ጋር የመኖር ጉጉትም በተቃራኒው አለች።

ሞትን በመኖር ጉጉት የፈራው ደጉ፣ “እባካችሁ መሞቴ ካልቀረ አንድ ነገር ተናግሬ ልሙት ደጉ ጥኢጦ እባላለሁ። የሀዲያ ልጅ ነኝ። እናቴ ሀሸቦ አንጀሎ ትባላለች። አንድ ነገር ተናግሬ ብቻ ልሙት . . . ክላሽ ጠመንጃን እንኳ የተማረ ሰው ነው መተኮስ የሚችለው። እኔ ሁለት ሜትር እንኳን ዘሎ የመውረድ ስልጠና የለኝም። ከአየር ላይ፣ ከኤሌኮፕተር ላይ ዘለህ ውረድ ተብዬ እምቢ ስላልኩ ነው ለግድያ የቀረብኩት. . .”

ሰራዊቱ “ፍቱት! ፍቱት ይፈታ ይፈታ!” ጮኸ። ጩኸት ከነጐድጓድ ያይል ነበር። ተፈታ። “ና ወደኛ! ግባ ወደኛ!” እያለቀሰ ሰራዊቱን ተቀላቀለ።

‘‘…ከዚህ በኋላ ካምፕ ውስጥ መኖር ጀመርኩ። ለጊዜው የተፈታሁ ቢሆንም ስጋት ነበረኝ። ይሁንና ከካምፕ መውጣት መግባት አልተከለከልኩም። አስመራ ከተማ ውስጥ እየሄድኩ ላውንቸር ቢራ እጠጣ ነበር።

‘‘አንድ ቀን ይህንኑ ቢራ ጠጥቼ ወደ ካምፕ በመመለስ ላይ እንዳለሁ አስመራ ከተማ ላይ የተኩስ እሩምታ ተከፈተ። ከተማዋ በላውንቸር ጥይት ትደበደብ ጀመር። ከምሽቱ 5 ሰዓት ነው። ወደ ካምፕ ልገባ ስጣደፍ መንገድ ላይ ወታደሮች አስቆሙኝ። ወታደሮቹ ሻዕቢያዎች ናቸው።

‘ቁም! ቁም! ምን ይዘኻል’

‘ሽጉጥ ይዣለሁ’

‘ስምህን ተናገር ’

‘ደጉ’

‘በል ፊትለፊት ያለውን መንገድ ይዘህ ዝም ብለህ ሂድ! ’

መንገዱን ይዞ መራመድ ጀመረ። መልሰው ደግሞ፣ ‘‘ቁም! ቁም!” አሉት።

“ምን ዓይነት ስቃይ፣ ምን ዓይነት ኑሮ ነው የኔ ኑሮ! ቁም፣ ቁጭ በል። አንዱ ኢሀፓ ነህ ይለኛል። ሌላው ደግሞ ከኤሌኮፕተር ዝለል ይለኛል። ከዚህ የስቃይ ኑሮ በቃ ገላግሉኝ። ግደሉኝ”

“ኢሀፓ ነህ እንዴ”

“አይደለሁም”

“አንተን ያሻንን ማድረግ እንችላለን”

“አድርጉኝ የፈለጋችሁትን። ምን የተመቸ ኑሮ አለኝና ነው አታድርጉ የምለው”

“ይህን ያህል የሚያማርርህና የሚያበሳጭህ ጉዳይ ምንድን ነው። ተቀመጥ እስኪ?”

ተቀመጠ። የማግባባት ስራ ተሠራ። ካግባቡት በኋላ የኋላ ታሪኩን ነገራቸው። ከዚህ በኋላ ጥያቄ ጠየቁት፤

“ገብረ መስቀልን ታውቃለህ?”

 

“አውቀዋለሁ። የኢሀፓ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል ነው። ቢያየኝ ደጉ ብሎ ይጠራኛል”፣ ሲል መለሰ።

ደጉ ከዚህ በኋላ የህዝባዊ ሀርነት ኤርትራ ማህተም ያለበት ወረቀት ተጽፎ ተሰጠው። “ይህን ወረቀት በኮሌታህ ውስጥ፣ ስትፈልግ ሙታንታህ ውስጥ … እኛ በፈለግነው ሰዓት፣ በፈለግንህ ቦታ መጥተን እናገኝህና መረጃ ትሰጠናለህ” አሉት።

መረጃ ማቀበሉ ቀርቶ ለውጊያ እንዲሠማራ የተጠየቀ ቢሆንም በውጊያ አላማው ላይ እምነት ስላልነበረው መዋጋት አልፈለገም። የሱ አላማ ከእነርሱ አላማ ጋር የማይገናኝ ነው። ዕምነታቸው እምነቱ አልነበረም። በዚህ ምከንያት ወደ ሱዳን ጠረፍ ተወሰደ። እዚያ አትክልት በሚለማበት ስፍራ አተክልት እያለማ አራት ዓመት ያህል ቆየ።

የኢትዮጵያ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ/ኢህዴን/ መመስረቱ ተነገረ- ሱዳን ጠረፍ ላይ እያለ። ኢህዴንን እንደሚቀላቀል ተገለፀለት። ለኢህዴን ከተሰጡ ሌሎች 34 ጓደቹ ጋር በመሆን እየተዋጋና እየተከላከለ አንገረብ ደረሰ። ኢህዴንን ተቀላቀለ።

. . . ይሰማኛል ያለፈው ህይወቴ ፣

የስቃይ ስብስብ ብሶቴ ፣

ለደርጐች ዕድሜ መስዋዕቴ ፣

ያበቃል ከእንግዲህ ልፋቴ …

ዜማ ከግጥሙ ጋር ህብር ፈጥሮ፣ አንጀት የሚበላውን ይህንን የህብር ድምጽ ከሚዘምሩት የደቡብ ታጋዮች መካከል ሌላኛው ታጋይ/ኮሚሽነር/ ታደሰ ጉርሜሳ ናቸው። እኚህ ሰው ከትግል በኃላ በተለያዩ የኃላፊነት እርከኖች ላይ ሰርተዋል። በፌዴራል ፖሊስ ውስጥ በኮሚሽነርነት ማዕረግ አገልግለዋል። በደቡብ ሱዳን አብዬ ግዛት የሰላም አስከባሪነት ግዳጃቸውን አጠናቅቀው በክብር ተመልሰዋል።

ታጋይ ታደሰ ጉርሜሳ አዲሰ አበባ ውስጥ የትራፊክ ፖሊስ ነበሩ- በደርግ ስርዓት። በወቅቱ ለስርዓቱ ዘብ እንዲቆሙ ግዴታ ተጥሎባቸው ወደ ኤርትራ ተላኩ። ቀድሞውኑም የስርዓቱ ጭቆናና ግፎች ያላንገፈገፈው አልነበረምና፣ ቢኖርም መውጫ ቀዳዳው ጠፍቶት ታፍኖ ቆይቷልና፣ ማምለጫ ቀዳዳ ሲገኝ የስርዓቱን እግር ብረት ሰብሮ መሄድ ምርጫ ነበር። ለታጋይ ታደሰና ከርሳቸው ጋር በዚህ ውሳኔያቸው ሀብረት ለፈጠሩት ሌሎች አራት ወጣቶች የእግር ብረቱን ሰብሮ ማምለጥና ከታጋዮች ጋር መቀላቀል ደስታ ነበር።

እናም አራት ሆነው፣ ከደርግ ወጥመድ አምልጠው ሻቢያን ተቀላቀሉ። ሻቢያን ሲቀላቀሉ ምርጫዎች ቀርበውላቸዋል። የመጀመሪያው ምርጫ ወደ ውጭ ሀገር መውጣት፣ ሁለተኛው ምርጫ መታገል፣ ሦስተኛው ምርጫ ወደ ደርግ መመለስ ነበር። የወጣቶቹ ምርጫ ትግል ሆነ።

ከዚህ በኋላ ሻቢያ ለህዋሀት አስተላለፋቸው። ህዋሀት ተደራጅተው ወደሚታገሉበትና ህብረ ብሄራዊነት ወዳለው ኢህዴን መራቸው፡፡ የዛኔው ታጋይ ታደሰ ጉርሜሳ በዚህ ዓይነት ሂደት በ1976 ዓ/ም ኢህዴንን ተቀላቀለ። ደርግ እስኪደመሰስ ድረስ ከጋዶቹ ጋር ተዋደቀ።

ታጋይ ታደሰ ጉርሜሳ በትግል ወቅት ያሳለፏቸውና ዛሬም ድረስ የማይረሷቸው ትዝታዎች አሏቸው፡-

“6ኛው የኢህዴን ድርጅታዊ ጉባኤ ሊካሄድ በተቃረበበት ወቅት ነው። ድርጅታዊ ጉባኤ ሊካሄድ በተቃረበበት ወቅት አንድ የደርግ ሀይል መደምሰስና አካባቢው ነፃ መውጣት አለበት።

በዚህ መሠሠረት ለውጊያ ተንቀሳቅሰን። ከአርማጨሆ ጐንደር መግቢያ ሲል ከፍተኛ ተራራ አለ። ተራራውን ወጥተን በመዋጋት የመደምሰስ ሥራ ማከናወን ነበረብን። ሀይከል ለመድረስ ከፍተኛውን ተራራ ስንወጣ ነጋብን። ያንን ከፍተኛ ተራራ ወጥተን ወደኋላ ተመለሱ ተባልን። አርማጫሆ ተመለስን፦

“ሄደን ስንመለስ ከፍተኛ ድካም ደርሶብናል። ድካሙን ለማገገምና የስነልቦና፣ የስንቅ ዝግጅት ለማድረግ 7 ቀናት ወሰደብን። ከ 7 ቀናት በኋላ ተመልሰን ወደ አውደ ግንባሩ መጣን። የአይከል ከተማን ከደርግ ነፃ አወጣን። የደርግ ኃይል ተደመሰሰ። ጉባኤያችንን ከአይከል ህዝብ ጋር አደረግን ….’’

ታጋይ ታደሰ ጉርሜሳ በትግል ጊዜያችው የማይዘነጉትና ከባድ የውጊያ ፈተና የነበረበት ከአላማጣ እስከ ደሴ ያለው ግንባር ነበር። ታጋዮች በዚህ ውጊያ ላይ ውሎ ለማድረግ 14 ቀናት ተጉዘዋል - ስንቅና ትጥቅ ተሸክመው። የ14ቱን ቀናት የጉዞ ድካም ሳይቀንሱ ነበር ወደ ውጊያ የገቡት። ውጊያው ከአላማጣ እስከ ደሴ ከተዘረጋው 605 ኮር የደርግ ሰራዊት ጋር ነበር።

ለዚህ የውጊያ አውደ ድንበር ላይ አቶ ታደሰ የሎጅስቲክ ጠርናፊ ነበሩ። በዚህ አውደ ግንባር የተደረገው ውጊያ ፈተና የበዛበት ነበር። ከትግሉ ኃይሎች የተሰጠ ተልዕኮ አለ። ተልዕኮው ወልዲያ ላይ ያለውን መተላለፊያ ዋሻ በመዝጋት ኮሩ ሬሽን እንዳያገኝ አድርጐ መቁረጥ ነበር። በዚህ የትግል ወቅት ነው ከደርግ በተተኮሰ አረር ፊታቸው የነበረ በሬ ተመቶ ሲሞት እርሳቸው ለጥቂት የተረፉት።

ይህን ተልዕኮ በድል ተወጥተው በጀነራል ኃይሌ አማካኝነት ቆቦ እንዲገቡ ታዘዙ። በጀነራል ኃይሌ አመራር ሰጪነት ከወልዲያ ቆቦ እየተጓዙ ሰማዩን የበረገደ፣ መሬትን ያንቀጠቀጠ ኃይለኛ ዝናብ ዘነበ። በድካም ላይ የዝናብ ዱላ ወረደባቸው። ጐርፍ ላይ ተቀመጡ። ጐርፍ ላይ ተኙ። ቆቦ ገቡ ፈተናዎቹን አልፈው።

የደቡብ ታጋዮችን ውሎ እያወጋን ነው። እያወጋንም ደርግን ለመጣል በተደረጉት እልህ አስጨራሽ የውጊያ ውሎዎች ላይ የደቡብ ታጋዮች እንደሌሉ፣ መስዋዕትነት እንዳልከፈሉ፣ ከዚህ ይልቅ የድል አጥቢያ አርበኞች እንደነበሩ አድርጐ የማቅረብ አዝማሚያዎች ይስተዋላሉ። ይህ ነገር እውነት ነው ?

ታጋይ ደጉ ጥኢጦ ኢህአዴግን ከተቀላቀለ በኋላ በተለያዩ የውጊያ አውደ ግንባሮች ላይ ተሰልፏል። ውጊያውን የተካፈለው ግን በሄራዊ ማንነቱን እንደያዘ ነበር። በእነዚህ ታሪካዊ የውጊያ ግንባሮች ላይ ግንባሩን ለትግል ሰጥቷል፡-

 

“የደርግ አውሮፕላኖች በቦንብ ሐሙሲትን ሲደበድቡ እኔ ነበርኩ። ሰውን፣ ውሻውን፣ አህያውን፣ እህሉን፣ አፈሩን፣ አውሮፕላኑ በቦንብ አንድ ላይ አደባልቀው። ሰው ነው ብለህ እንዳታነሳ ስጋ ነው። ውሻውም ስጋ ነው። አህያውም ስጋ ነው። ሁሉም ስጋዎች ናቸው። ከብቱም ስጋ ነው። ተደበላልቋል። አሞራ፣ አይናችን እያየ የሰውን ስጋ ከእንስሳ ስጋ ጋር ቀላቅሎ በላ። ፈተናው ከባድ ነበር።

“እኔ በበለሳው ውጊያ ላይ አመራር ነበርኩ። በለሳ፣ ጨውጨዋት፣ ዞዛምባ፣ ቋልሳ . . . በሙሉ ነፃ ወጥተዋል፡፡ ህዝቡን የማረጋጋት ስራ እየሠራን ነበር። የኢህዴንን ዓላማና ፕሮግራሞች እናስተምራለን። እያስተማርን እንዋጋለን በግልም፣ በቡድንም፣ በኃይልም፣ በጋንታሞ፣ በሌሎችም

“ሽምቅ ውጊያ መለያችን ነበር። ደርግም ይህንኑ ስልት መጠቀም ጀምሮ ነበር፡፡ በለሳ ላይ በ1979 ዓ/ም የሽምቅ ውጊያ በምናደርግበት ወቅት ህዝቡ ተገን ሆኖ ከኛ እኩል መስዋዕትነት ከፍሏል።

“አንዲት እናት ነበሩ። አንድ ዕለት እኚህን እናት፣ ‘የሰርጉዴ እናት ምነው ዛሬ በሌሊት ተነስተው ይቦ ይጋግራሉ?’ አልኳቸው። ‘የገበያ ዕለት ስለሆነ ነው። ይልቅ እቤት ግባና ከህፃኗ ጋር ተጫወት’ አሉኝ። ምን ማለት ነው በሚል ድንግጥ አልኩኝና ማጣራት ሳደርግ ለካ የደርግ ሸማቂዎች ዙሪያዬን ከበውኛል። ክላሼን እንደፈታሁ ነበር። በመካከላችን ያለው ርቀት 10 ሜትር ያህል ነበር። ‘ቁም!’ አልኩኝ። እነርሱ በፊንታቸው ‘አይዞህ! አብቅቷል። እጅ ስጥ እጅ ስጥ ’አሉኝ። ሁለቱንም አዚያው ሳይነቃነቁ አስቀረኋቸው። ለብቻዩ ቀኑን ሙሉ ተዋግቼ ሁለት ገድዬ፣ አንድ አቁስዬ አምስት ማርኬ ገባሁ። ይህ የአንድ ቀን ውሎዩ ነው…

 

ታጋይ ታደሰ ጉርሜሳም በትግሉ ውስጥ ከባድ መስዋዕትነት የከፈሉ ሌሎች የደቡብ ልጆች መኖራቸውን ይናገራሉ፡-

“በኢህዴን ሠራዊት ውስጥ በርከት ያሉ የደቡብ ታጋይ ልጆች ነበሩ። አንድ ስሙን የማላስታውሰው የሀዲያ ልጅ ሁሌም አይረሳኝም። መትረየስ ተኳሽ ነበር። ኃይለኛ ነበር። ጠንካራና ጀግና ታጋይ ነበር። ትዕዛዝ ጥሶ ነበር ወደ ውጊያ መሀል የሚገባው።

ደረቱን በጥይት ተመቶ ነው ያለፈው። ለደርግ እጅ ላለመስጠት ሲል ‘እባካችሁን ጨርሱኝ፣ ትታችሁኝ አትሂዱ! ያለን አንድ የወላይታ ታጋይ ጓድ ዛሬም ድረስ የዛን ጊዜ ሁኔታው ይመጣብኛል። ይህንን ያለው በደርግ እጅ ላለመውደቅ ነበር።

ታጋዮች ይዘምራሉ

ኢትዮጵያ ለምለሟ ሀገሬ ፣

ብረካም ካንቺ መፈጠሬ ፣

ፋሲሽቱ ወንድሞቼን በልቶ፣

ተሰምቶኛል ዛሬ ግፉ በዝቶ፣

ታጋይ  ከበደ ካሚሶ ይባላሉ። በሐዋሣ ከተማ ምክርቤት ውስጥ የህግ ባለሙያ ናቸው። ይህንኑ መዝሙር ከታጋይ ጓዶቻቸው ጋር ይዘምራሉ።

የደርግ መንግስት ነው ከሚማሩበት ክፍል ውስጥ ወስዶ ለብሄራዊ ውትድርና አገልግሎት ያሰለፋቸው። የብሄራዊ ወትድርና ስልጠና ተሰጥቷቸው ትግራይ ተመደቡ። በኋላ ግን ደርግን ትተው አብዮታዊ ዴሞክራሲ ሀይሎችን ተቀላቀሉ።

በትግል ህይወታቸው ውስጥ በርካታ አሳዛኝ ጊዜያቶችን አሳልፈዋል፡፡ ከእነዚህም ውስጥ የማይረሱት ጊዜ አለ። የማትረሳው ያች ጊዜ ፣ ያች ዕለት በታጋይ ካሚሶ ከበደ አይምሮ ውስጥ ያስቀመጠችው ጠባሳ አለ።

አካባቢው ተከዜ ነው። ተከዜ በረሀ ውስጥ የደቡብ ታጋዮች ከኢህዴን ወጥተው የራሳቸውን ድርጅት መስርተው የመንቀሳቀስ እድል ባገኙበት ወቅት የተሰማቸውን የደስታ ስሜት ለመግለጽ ሰልፍ የወጡበት ነበር። ሰልፉን የሚመለከት፣ የሰልፈኛውን የመፈክር ድምፆች የሚሰማ ህዝብ ከጐንና ጐናቸው አልነበረም - ከበረሀ ዛፎች በስተቀር። ከሰማዩ በስተቀር። ከረገጧት መሬት በስተቀር፣ ከወፎችና አሞራዎች በስተቀር። በረሀውን ሰንጥቆ ከሚነጉደው የተከዜ ወንዝ በስተቀር። አይደለም። ሌላም ሰለማዊ ያልሆነ፣ የደርግ ሰው በላ የሰማይ ላይ የብረት አሞራ ነበር። የደርግ ጦር አውሮፕላን።

ታጋዮቹን ያስደሰታቸው በወቅቱ የነበሩትን የትምክህተኝነት፣ የበታችነት እንዲሁም የማንነት ጥያቄዎች በውስጣዊ ትግል ከተራማጅ የሌሎች ብሄር ብሄረሰብ ታጋዮች ጋር ባደረጉት ትግል ያገኙት ሌላም ድል ነበር። ለዚህ ድል ነበር ተመልካች ህዝብ፣ ሰሚ የሰው ስብስብ በሌለበት፣ ወፍና ቁራ በሚጮህበት የተከዜ በረሃ ላይ ሰልፍ ማካሄዳቸው።

በዚያ ሰልፍ ላይ ነው ከህሊና የማይፋቀውን ቁስል ሰው በላዎቹ የብረት አሞራዎች የፈፀሙት። በአውሮፕላኖቹ፣ በጠላት ተከታታይ የቦንብ ውርጅብኞች፣ 12 የደቡብ ታጋዮች ተሰው። አስክሬናቸው ተለቅሞ እንዳይነሳ አድርገው አውሮፕላኖቹ በቦንብ ደበደቧቸው።

ስጋዎቻቸውን ቆራርጠው፣ አጥንቶቻቸውን ፈጭተው፣ ለበረሀው መሬትና አሞራ ረጯቸው። ያ ሁሉ ዘግናኝ ድርጊት እየፈተፀመም፣ የሚሞተው እየሞተም ሰልፉ ቀጥሏል። ታጋዩ “የደርግ ጭፍጨፋ እስከ ግብዓተ መሬቱ ነው!” ፣ “ እስከ ግብዓተ መሬቱ ነው!”

 

በአጠቃላይ የደቡብ ታጋዮች ከሌላው ታጋይ እኩል ለትግሉ ላባቸውን አንጠባጥበዋል፣ ደማቸውን አፍሰዋል። መስዋዕት ሆነዋል።  የደቡብ ልጆች የደርግን ስርዓት በመደምሰስ ሂደት ውስጥ የነበራቸውን ሚና አቅሎ መመልከት አይቻልም። አይናቸው ጠፍቷል። አካላቸው ጐሏል። ሞተዋል። ዛሬ ከደኢህዴን ወጥተው በከፍተኛ አመራርነት ላይ ለሚገኙት ጓዶች መሠረት የሆኑት እነዚህ ታጋዮች ናቸው።