ደኢህዴን የተመሰረተበትን  ሃያ አምስተኛ ዓመት   አስመልክቶ  ከደኢህዴን ማዕከላዊ ኮሚቴ ጽህፈት ቤት የተሰጠ መግለጫ

ደኢህዴን የተመሰረተበትን  ሃያ አምስተኛ ዓመት   አስመልክቶ  ከደኢህዴን ማዕከላዊ ኮሚቴ ጽህፈት ቤት የተሰጠ መግለጫ

    

አገራችን ኢትዮጵያ በተፈጥሮዋ  የብዙ ቋንቋዎች፣  ባህሎች፣ ሃይማኖቶች ፣ ወጎች እና   ታሪኮች  ባለቤት ናት፡፡ ይሁን እንጂ  እነዚህን ብዝሃነቶች ከመቀበል፣ ከማስተናገድና   ለአገር ግንባታም እንደመልካም ዕድል ከመጠቀም ይልቅ ብዝሃነቶቹ ህልውናቸውን እንዲያጡና እንዲደፈጠጡ ፤ ህዝቦችም ለስነ- ልቦናዊ ቀውስ እንዲጋለጡ   መንግስታዊ ጭቆና ሲያሳርፉባቸው ቆይተዋል፡፡  የህዝቦች ዴሞክራሲያዊና ሰብአዊ መብቶች  እንዲገፈፉና እንዲገረሰሱ አድርገዋል፡፡ ሠፊው ህዝብ ከኢኮኖሚው ተጠቃሚ እንዳይሆንም አድርገዋል፡፡ በአጠቃላይ የቀድሞዎቹ ጨቋኝ መንግስታት ከጨቋኝ ባህሪያቸው በመነሳት የብሔር ብሔረሰብና  የሃይማኖት እኩልነት እንዳይረጋገጥ፣ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት በተለይም የመሬት ባለቤትነትን በመንፈግ ሰፊው ህዝብ በድህነት አረንቋ እንዲማቅቅ  አድርገዋል፡፡ ዴሞክራሲያዊና ሰብአዊ መብቶችም  በግላጭ  እንዲረገጡ አድርገዋል፡፡

የደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦችም   ብሔራዊና መደባዊ  ጭቆናዎች  ተጭነውባቸው በአሳማሚና በሚዘገንን ሁኔታ ረጂም ዘመናትን በሰቆቃ አሳልፈዋል፡፡ የክልሉ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች  የየራሳቸው የሆነ ጥንታዊ የራስ ገዝ አስተዳደር የነበራቸው ቢሆንም በተለይም ከዳግማዊ ሚኒልክ ወረራ በኋላ ይህን ራሳቸውን የሚያስተዳድሩበትን  ስርዓት በኃይል እንዲያጡት ተደርገዋል፡፡ ቋንቋቸው ፣ ባህላቸው ፣ አጠቃላይ ስነ-ልቦናቸውና ሰብዕናቸው  እንዲናጋ ሆኗል፡፡

ራሳቸውን በራሳቸው ሲያስተዳደሩበት  የነበረው ሥርዓታቸው ተወግዶ በጨቋኝና በዝባዥ አገዛዝ ሥር ወድቀዋል፡፡ በተፈጠሩበት፣ በኖሩበትና ባለሙት መሬት የባለቤትነት መብት ተነፍገው ለገባርነትና ለጢሰኝነት ተዳርገዋል፡፡ የህልውናቸው መሠረት የሆነውን ባህላቸውን፣ ቋንቋቸውንና እምነታቸውን እንዲተውና እንዲክዱ ተገድደዋል፡ይሁን እንጂ የደቡብ ህዝቦች ነፃነታቸውን ላለማስነጠቅና ግዛታቸውን ላለማስደፈር መጠነ ሰፊ የመከላከል ተጋድሎ ፈጽመዋል፤ ጭቆናን አሜን ብለው ላለመቀበል  ሲፋለሙ  በርካታ የክልሉ ዜጎች መሰዋዕትነት ከፍለዋል፡፡

በህዝቦች ጫንቃ ላይ ተጭኖ ለዘመናት የዘለቀው አፄአዊ የጭቆና ስርዓት  በ1966ቱ ዴሞክራሲያዊ አብዮት የተገረሰሰ ቢሆንም ትክክለኛና የተደራጀ  መሪ ሀይል ባለማግኘቱ ምክንያት መክኗል፡፡ የዴሞክራሲያዊ አብዮት  ንቅናቄው ያነገባቸውን የብሔርና የሃይማኖት እኩልነት፣ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት /የመሬት ባለቤትነት/ እንዲሁም የዴሞክራሲያዊና ሰብአዊ መብት ጥያቄዎችን በአግባቡ የሚመልስ የተደራጀ መሪ  ሀይል በወቅቱ ባለመዘጋጀቱ ምክንያት  ህዝባዊ ትግሉ  ሳይመታ ቀርቷል፡፡ በዚህም የተነሳ  በመላው የአገርቱ ክፍሎች የፊውዳሉን ሰርዓት  ጠጋግኖ ያስቀጠለውን ደርግን መፋለም ተጀመረ፡፡ የትግሉ ሂደት በተለያየ መልኩ ቀጠለ፡፡  በፀረ ደርግ   ትግል ሂደት የደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች የፀረ ጭቆና ትግል ተጠናክሮ እንዲቀጥል ሆኗል፡፡ ይልቁንም ከሌሎች አብዮታዊና ዴሞክራሲያዊ ኃይሎች ጋር በመሆን ትግሉ  ተጠናክሮ ቀጥሎ የተደራጀ መሪ ሀይል እስከመፍጠርና ህዝቡንም በተደራጀ አግባብ የማንቃትና የመምራት ተልዕኮውን ወደ መወጣት ተሸጋግሯል፡፡

የክልሉን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ፀረ-ጭቆና ትግል  በተደራጀ አግባብ የመምራቱን ተልዕኮ ከመወጣት አንፃር  የስምጥ ሸለቆ ታጋዮች መሸጋገሪያ ማህበር ያበረከተው አስተዋጽኦ ሁሌም በታሪክ  ሲታወስ የሚኖር ነው፡፡ ከደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች አብራክ የወጡ ታጋዮች በኢህዴንና በህወሓት እህት ድርጅቶች ታቅፈውና ተደግፈው እየበቁ ፣ በሂደትም ራሱን የቻለ አታጋይ አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት እንዲመሰረት እርሾ በመሆን በርካታ አብዮታዊያን ታጋዮች አንዲፈጠሩ ፣  ሚሊየኖች ደግሞ  በዙሪያቸው  እንዲሰባሰቡ በማድረግ    ለዛሬው  ስኬት እንድንበቃ አድርገዋል፡፡

  በስምጥ ሸለቆ ታጋዮች መሰረቱ  የተጣለው የደቡብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ- ደኢህዴን በየምዕራፉ ያጋጠሙትን ፈተናዎች በትግል እየተራመደ ፣ ከፈተናዎቹም እየተማረ የሃያ አምስት ዓመታት  የትግልና የድል ጉዞዎችን ተጉዟል፡፡ የደኢህዴን ጉዞዎች በመጠነ ሰፊ ስኬቶች የታጀበ፣የክልላችንን የማሽቆልቆል ጉዞ የገታ፣ ብዝሃነትን የመቀበል ፣ የማክበርና  የማስተናገዱን  ሂደትም በአስደናቂ ሁኔታ  እዲጎለብት ያስቻለ ሆኗል፡፡

በክልሉ የሚገኙት 56 ብሔሮችና  ብሔረሰቦች  ተቀራራቢ ሥነ-ልቦና ያላቸው፣ ዘመናትን የተሻገሩ የጋራ እሴቶችን  የገነቡ፣  ብሔራዊና መደባዊ ጭቆናዎች የተጫኑባቸው እንዲሁም ከፍተኛ የሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች መገርሰስ የደረሰባቸው በመሆናቸው ክልላዊ አንድነቱን በማጠናከር በመፃኢ ተስፋቸውና እድገታቸው ላይ በጋራ ለመቆም ወስነው ተንቀሳቅሰዋል፡፡

ባለፉት ሃያ አምስት ዓመታት ብዝሃነትን በአግባቡ ሊያስተናግድ የሚችል ዴሞክራሲያዊ ስርዓትበመዘርጋቱ ምክንያት የህዝቡ የዘመናት ጥያቄዎች ትክክለኛ ምላሽ ማግኘት ችለዋል፡፡ በተለይም  የያኔው ደኢህዴግ  የአሁኑ ደኢህዴን ከተመሰረተበት መስከረም 29 1985 ጀምሮ በተደረጉት ሁሉአቀፍ ጥረቶች አስደናቂ  ስኬቶች ተመዝግበዋል፡፡ እየተመዘገቡም ይገኛሉ፡፡  በዚህም መሠረት የብሔር ፣የብሔረሰብና የሃይማኖት እኩልነት፣ ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ህገ-መንግስታዊ ዋስትና አግኝተዋል፡፡   ራስን በራስ የማስተዳደር፣ በአካባቢ የመልማት አቅሞች ላይ ተመስርቶ እድገትን ለማፋጠን የሚያስችል እኩል ዕድልና ፍትሃዊ ተጠቃሚነትን ያሰፈነ ስርዓት ባላቤት ሆነዋል፡፡

የክልላችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በቋንቋቸው፣በባህላቸው ፣ በታሪካቸው እንዲኮሩ ፣የሥነ-ልቦና ሀሴትም እንዲጎናፀፉ የሚያስችል ምቹ ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡ በቋንቋቸው የመማር፣የመዳኘት፣የጽሁፍ መግባቢያ የማድረግ ዕድሎች ተዘርግተዋል፡፡ በዚህም መሰረት በክልሉ በ29 የብሔር ብሔረሰብ ቋንቋዎች የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት እየተሰጠ ያለ  ሲሆን አምስት የብሔር ብሔረሰብ ቋንቋዎች ደግሞ በክልሉ ውስጥ በሚገኙ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት  እንደ አንድ የትምህርት አይነት ፕሮግራም ተቀርፆላቸው እየተሰጡ ይገኛሉ፡፡

ደኢህዴን የህዝቦችን የዴሞክራሲ ፣ የሠላምና የልማት ጥያቄዎችን ለመምራትና በህዝቡም የነቃ ተሳትፎ ጥያቄዎቹ እንዲመለሱ የማድረግ ተልዕኮን ያነገበ ድርጅት ነው፡፡ ስለሆነም ጥያቄዎቹ የህዝቡን የነቃ ተሳትፎ ከማረጋገጥ ውጭ ሊፈቱ እንደማይችሉ ያምናል፡፡ ስለዚህም የሰፊውን ህዝብ የነቃ ፣ነፃና ዴሞክራሲያዊ ተሳትፎ ለማረጋገጥ በትኩረት ተንቀሳቅሷል፡፡ በዚህም ህዝቡ በቀጥታና  በየደረጃው በሚገኙት የህዝብ ምክር ቤቶች በሚመርጣቸው/በመረጣቸው ተወካዮቹ አማካኝነት እየተሳተፈ ይገኛል፡፡

ከደኢህዴን /ኢህአዴግ ስኬቶች መካከል የመደብለ ፓርቲ ስርዓትን እውን ማድረግ መጀመራችን   አንዱ ሲሆን ሉአላዊ የስልጣን ባለቤትም ህዝቡ እንዲሆን በተዘረጋው ህገ መንግስታዊ ስርዓት መሰረት  እንደ አንድ ፓርቲ ለህዝብ ቀርቦ እየተወዳደረ ስልጣን በህዝቦች ይሁንታ የሚሸጋገርበት ስርዓት መሰረት እንዲጥል አድርጓል፡፡

ደኢህዴን ከህዝባዊ ባህሪው በመነሳት ልማታዊ መልካም አስተዳደርን እያረጋገጡ መሄድ  ጉዳይ የሞት ሽረት ጉዳይ በማድረግ እየተንቀሳቀሰም ይገኛል፡፡ ልማታዊ መልካም አስተዳደርን ከማስፈን አንፃር በርካታ ስኬቶች የተመዘገቡ ቢሆንም ድርጅቱ በጥልቅ ተሀድሶው ወቅት  ሰፋ ያለ ጉድለት አለባቸው ብሎ ከገመገማቸው መስኮች አንዱ ደረጃ በደረጃ የህዝብን እርካታ  የማረጋጋጥጥ  ጉዳይ በመሆኑ በቀጣይ  የተጠናከረ  ርብርብ ማድረግ ይጠበቅብናል፡፡

በኢኮኖሚ ልማቱ መሰክም ባለፉት ሃያ አምስት  ዓመታት  ስኬቶች ተመዝግበዋል፡፡ ግብርናና አርሶ አደርነትም የሀብትና የፀጋ ምንጮች እንጂ የጉስቁልና መገለጫዎች እንዳልሆኑ ገጠርንና ግብርናን  ማእከል ያደረገው  የደኢህዴን / ኢህአዴግ ፖሊሲና ስትራቴጂ  በተግባር አረጋግጧል፡፡

የግብርናው ዘርፍ የደርግ መንግስት ተገርስሶ መሪ ድርጅታችን ደኢህዴን /ኢህአዴግ ክልሉን መምራት በጀመረበት ወቅት የነበረው ሁኔታ ሲታወስ አርሶአደሩና አርብቶአደሩ ከድህነት ጋር ተፋቅሮና ተዋዶ የሚኖርበት፣ በኋላ ቀር አስተሳሰብ ተተብትቦ የሚሰቃይበት፣ ከራሱ ቤተሰብ ምግብ ፍጆታ ውጭ የማምረት አመለካከት፣ ክህሎትና አቅም ያጣበት፣ ከገበያ ጋር ግንኙት ያልነበረው ፣ ከዘልማድ የግብርና አመራር ውጭ መረጃ የማግኘት፣ እውቀት፣ የግንዛቤና የክህሎት ጉድለት የነበረበት፣ ድህነት ጋር ከመላመዱ የተነሳ ድህነቱን አምኖ የኑሮ አካል አድርጐ ተስማምቶ የሚኖር የተበተነ አርሶ አደር፣ በመሬቱ ወይም በይዞታው ላይ እምነት ያልነበረው፣ የኤክስቴንሽን ድጋፍ በበቂ ሁኔታ የማያገኝ፣ እንደነበረ ማስታወስ ይቻላል፡፡

በደኢህዴን የሚመራው የክልሉ መንግስት ይህንን አስከፊና ኋላቀር ሁኔታ ስርነቀል በሆነ መልኩ  በመቀልበስ ፣በመቀየርና አዲስና ህዝቦችን ከድህነት መንጭቆ የሚያወጣ ተጨባጭ ሁኔታ ፈጥሯል፡፡ የፀረ-ድህነት ትግሉ ከአስተሳሰብ እድገት የሚነሳ መሆኑን ተገንዝቦ ይህ ድህነትን  የመጠየፍ አንዲሁም በተግባራዊ ርብርብ የማሸነፉ   አስተሳሰሰብ  የመላው ህዝቦች አስተሰሳብና ባህል እንዲሆንም በቁርጠኝነት ተንቀሳቅሷል፡፡  ኢኮኖሚው በግብርና መሪነት በፍጥነት እንዲያድግ የአመለካካት፤ የክህሎት፤ የግብዓት፣ የእውቀት ፣ የአሰራር፣ የቴክኖሎጂ እድገት እንዲረጋገጥ ወሳኝ እርምጃዎችን ተራምዷል፤ በዚህም አስደናቂ ስኬቶች ተመዝግበዋል፡፡በክልል ደረጃ የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ ተችሏል፡ከዓመታት  በፊት በከፋ የድህነት  ቀጠና ውስጥ ይኖር  ከነበረው ህዝብ መካካል ግማሽ  ያህሉ    በተደረጉት ሁሉአቀፍ ጥረቶች  ከከፋው የድህነት ቀጣና ሊወጣ   ችሏል፡፡

 አርሶ አደሩ ዛሬ ሀብታምና  የኢንዱስትሪ ሽግግሩንም መምራት መምራት የጀመረበት ነባራዊ ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡    አርሶአደራችን  ለቤተሰቤ ፍጆታ ካመረትኩ ይበቃኛል ከሚለው አስተሳሰብ እንዲወጣና  የአመለካካት፣ የእውቀት፣ የግንዛቤና የክህሎት ችግሩ ቀስ በቀስ እንዲፈታ ማድረግ በመጀመራችን ቀጣይ የበለጠ መሥራት የሚገባን መሆኑ እንደተጠበቀ ዛሬ ሽጦ ማምረት የሚችልበት ደረጃ ላይ  እየደረሰ ይገኛል፡፡ ዛሬ የክልላችን አርሶ አደሮች ያላቸውን ፀጋ መሰረት በማድረግ ገበያ የሚፈልገውን፣ መጠን ጥራትና አይነትና ወቅት መሰረት ያደረገ የማምረት ሂደት ውስጥ በመግባት የመደራደር አቅማቸውንም በከፍተኛ ደረጃ በማሳደግ ላይ ይገኛሉ፡፡ በዚህም ባለፉት ሃያ አምስት ዓመታት በአጠቃላይ እና በተለይ ደግሞ ከዳግም ተሀድሶው በኋላ የፈጣን ዕድገት ባለቤት ሆኗል ፤ባለሁለት አሃዝ የኢኮኖሚ እድገትም ተመዝግቧል፡፡የዚህ የባለሁለት አሃዝ ፈጣን ዕድገት ዋነኛ ምንጭ ደግሞ ገጠርና ግብርና ሆኗል፡፡

 አጠቃላይ ክልላዊ ምርቱ  በ1986/87 ምርት ዘመን  በስንዴ አቻ ግምት ከ15 ሚሊዮን ኩንታል በታች ከነበረበት    እሰከ 2008/09 ምርት ዘመን  ድረስ ባሉት ዓመታት  በአሥር እጥፍ አድጓል፡፡ በተመሳሳይ የመስኖ ልማት ሽፋን በ1987   44 ሺህ 910 ሄክታር የነበረ ሲሆን  በ2009 በሁለቱም ዙር የመስኖ እንቅስቃሴ  523 ሺህ 923 ሄክታር  ማድረስ ተችሏል፡፡  ከሁሉም የግብርና ልማት ተግባራት  አንጻር ምርትና ምርታማነትን በከፍተኛ ደረጃ እያሳደጉ ያሉ በርካታ ሞዴል አርሶ አደሮችን መፍጠር ተችሏል፡፡  ይሁን እንጂ   በሞዴል አርሶ አደሮችና በክልላዊ አማካይ ምርታማነት መካከል  ያለው ልዩነት  አሁንም እጅግ ሰፊ በመሆኑ በቀጣይ ሰፈ ትግል እንደሚጠበቅብን  መረዳት ይገባል፡፡

ከተፈጥሮ ሀብት ልማትና ጥበቃ አኳያ    በየአመቱ 33 በመቶ  የክልላችን ህብረተሰብ  በማሳተፍ 4.5 ሚሊዮን ሄክታር  መሬት የስነ-አካላዊ ስራና    በቢሊየኖች የሚገመቱ  ዘርፈ ብዙ ችግኞችን በመትከል አካባቢያችን መጠበቅ የቻልንበትና ለአረንጓዴ ኢኮኖሚ ልማት  ግንባታው   ስኬት የበኩላችንን አስተዋጽኦ እያበረከትን እንገኛለን፡፡ ከዚህ ተግባር አንጻርም የሚታዩትን የጥራት ጉድለቶች ለማረም እንዲሁም  ችግኖችን ከመትከል ባሻገር የማጽደቅ ፣ የመንከባከብና የማሳደጉን ተግባር  በቀጣይ በትኩረት መፈጸም ይጠይቃል፡፡

 በክልላችን የሚገኙ ከፊል አርብቶአደሮችና  አርብቶአደሮች በክልሉ እየተመዘገበ ካለው ፈጣን ዕድገትና መልካም አስተዳደር ዉጤቶች ተጠቃሚ እንዲሆኑ መሠረታዊ አቅጣጫዎች በመንደፍ የአርብቶአደሩን ህይወት ለመለወጥ በሚደረገው ልዩ ትኩረት ዉኃን ማዕከል ተደርጎ የመንደር ማሰባሰብ ፕሮግራም የግቡ ማስፈፀሚያ ስልት ተግባራዊ እየተደረገ  ይገኛል፡፡  የመንገድ ፣ የንጹህ መጠጥ ዉሃ ፣ የማህበራዊ  አገልግሎት መሰጫ  ተቋማት ግንባታዎች  እየተከናወኑ ይገኛል ፡፡    በአጠቃላይ የአርብቶአደሩን ህይወት  ሁሉአቀፍ በሆነ መንገድ ለመቀየር  የተጀመረው እንቅስቃሴ ሰፋ ያለ ጥረትና ልፋት የሚጠይቅ መሆኑ ታውቆ በቀጣይ ሰፊ ርብርብ ማድረግ ወሳኝ ይሆናል፡፡

በአጠቃለይ ኢኮኖሚው በሂደት ከግብርና  የመሪነት ሚና ወደ ኢንዱስትሪው ዘርፍ መሪነት ደረጃ በደረጃ የሚሸጋርበት መደላድል እየተገነባ ይገኛል፡፡ በገጠርና በግብርናው ዘርፍ የተመዘገበው  አስደናቂ ስኬት እንደተጠበቀ ሆኖ  ሠፊ ጥረት የሚፈልጉ ማነቆዎች መኖራቸውን  በአግባቡ ተገንዝቦ   ማናቆዎቹን ለመፍታት መረባረብ  ተገቢ ነው፡፡   ስለሆነም  ሃያ አምስተኛውን ዓመት የምስረታ በዓል ስናከብር በቀጣይ ትኩረትና ትግል የሚጠየቀውንና ከምርታማነት አኳያ የሚታየውን ውስንነት  ለመቀልበስ የሞት ሽረት ትግል ለማድረግ ዳግም ቃል እየገባን ሊሆን ይገባል፡፡

 

በከተሞች ልማትንና መልካም አስተዳደርን ለማረጋገጥ  ባለፉት ሃያ አምስት ዓመታት በተደረጉት እንቅስቃሴዎች አበረታች  ውጤት  ተመዝግበዋል፤፡ ከ1985 በፊት በክላልችን የነበሩ ከተሞች ብዛት 149 ሲሆን በ2ዐዐ8 ዓ/ም ወደ 38ዐ ደርሷል፡፡ በአሁኑ ወቅት  የክልላችን የከተማ ህዝብ ዕድገት 19 በመቶ የደረሰ ሲሆን የህዝብ ዕድገት ምጣኔውም 5.4 በመቶ እንደሆነ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡   በከተሞች የሚኖሩ የስራ ዕድል ያላገኙ ዜጎቻችን በተለይ ወጣቶችና ሴቶች  ክህሎታቸው እንዲጨምርና አስፈላጊውን ግብአት በማቅረብ የስራ ዕድል ተጠቃሚ እንዲሆኑ በማድረግ በልማታዊና ዴሞክራሲያዊ መንግስቱ ሁሉአቀፍ ድጋፍና የቅርብ አመራር ሚሊዮኖች ልማታዊ ተግባር ውስጥ ገብተው ሃብት ማፍራት ጀምረዋል፡፡  ነገር ግን  ከተሞቻችን ለኑሮና   ለስራ ምቹ ፣  ድህነትን በወሳኝ መልኩ የሚቀለብስ  የስራና የገቢ  ማዕከላት አንዲሆኑ ከማድረግ  እንዲሁም  የልማታዊ ፖለቲካ ኢኮኖሚ የበላይነት እንዲረጋገጥባቸው ከማስቻል አንጻር ቀጣይነት ያለው ርብርብ ማድረግ ከሁሉም አካላት የሚጠበቅ   መሆኑንም ደኢህዴን ጥሪውን ያስተላልፋል ፡፡  

 

ደኢህዴን/ኢህአዴግ ለትምህርቱ ዘርፍ በሰጠዉ ትኩረት  በክልላችን የሚገኙ ብሔሮች፤ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ከትምህርት ፍትሃዊ ተጠቃሚ ለማድረግ፤ ክልሉንም ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ ያደረገዉ ትግል በስኬት ጐዳና ላይ ነው።  የትምህርት ቤቶችን ሥርጭት ኢፍትሃዊነት ለማስወገድ እያደገ የመጣው የትምህርት ቤቶች ቁጥር የሥርጭት ፍትሃዊነቱን ጠብቆ እንዲፈጸም የማያቋርጥ አመራር በመስጠትና አፈጻጸሙን በመከታተል በፆታ፣ በዞኖችና ልዩ ወረዳዎች፣ በብሔረሰቦች፣ በከተማና በገጠር በተለይም በአርብቶአደር አካባቢዎች ያለው የትምህርት ተሳትፎ ልዩነት ለማጥበብ የተደረገው ትግል አስደማሚ ውጤት አስገኝቷል፡፡ ነገር  ግን የትምህርት  ጥራትን ለማረጋገጥ የተቀረጸውን  ፓኬጅ በተሟላ ሁኔታ ተግባራዊ ከማድረግና ብቁ ፣ተወዳደሪና የህዳሴውን ጉዞ ሊያቀላጥፍ የሚችል ትውልድ የመቅረጹ ስራ  በቀጣይ  የሁሉንም ርብርብ የሚሻ በመሆኑ በትኩረት መንቀሳቀስ ተገቢ ይሆናል፡፡

በጤና ፖሊሲው በመመራት የክልላችን ህዝቦች በተለይም  ደግሞ ሴቶችና ህጻናት ላይ በማተኮር እንዲተገበር የማስፈፀሚያ መንገዶችን ጭምር በመቀየስና ተግባራዊነታቸዉን በጥብቅ በመከታተል በደኢህዴን የሚመራው መንግስት  ቁልፍ ሚና ተጫዉቷል፡፡  በ1987  28 በመቶ ወይም በጤና ጣቢያ ስታንዳርድ ከ10 በመቶ በታች የነበረዉ የክልሉ የመሰረታዊ ጤና አገልግሎት ሽፋን 95 ከመቶ ማድረስ የተቻለ ሲሆን የምዕተ ዓመቱን የልማት ግብ ማሳካትም ተችሏል፡፡ እድሜያቸው ከ5 ዓመት በታች የሆኑ ህፃናት ሞት በ1992/93 ዓ.ም 191 በ1000 ከነበረበት ወደ 64 ዝቅ በማድረግ የምዕተ ዓመቱን ግብ 3 ዓመት አስቀድሞ ማሳካት ተችሏል፡፡ በአጠቃላይ በዜጎች ጤናና ኑሮ ላይ ከፍተኛ መሻሻል በመኖሩ አማካይ የእድሜ ቆይታም በ1983 ዓ.ም 42  ዓመት  ከነበረበት በአሁኑ ወቅት 65 ዓመት ማድረስ ተችሏል፡፡

በመሰረተ ልማት ዝርጋታው ረገድም  በደኢህዴን የሚመራው መንግስት በተሳካ ሁኔታ ተራምዷል ፡፡ በመንገድ ፣ በንጹህ ውሃ አቅርቦት፣ በቴሌኮም ፣ በመብራ ሀይል አቅርቦት ረገድ እምርታዎች የተመዘገቡ ቢሆንም እየደገ ከሚቀጥለው ህብረተሰባዊ አዳጊ ፍለጎትና እያጋጠመው ካለው የመልካም አስተዳደርና የአገልጋይነት መንፈስ መጓደል የሚመነጩ ችግሮች በርካታ በመሆናቸው አነዚህን ሁኔታዎች ለማረም መረባረብ ይገባናል፡፡

ባለፉት 25 ዓመታት አብዮታዊና ዴሞክራሲያዊ ድርጅታችን ክልሉን በስኬት ጐዳና ማራመድ  የቻለ ቢሆንም ከተግዳሮቶች ግን ነፃ አልነበረም፡፡   የጥገኝነት ወይንም  የኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከቶችና ተግባራት በተለያየ መልኩ እየተፈታተኑን ፣  አደናቃፊነታቸው አሁን ከሚታየው በላይ  ጉዳት እንዳያደርስም በትግል እየመከትናቸው  የድል ጉዟችንን  ቀጥለናል፡፡   በጀመርነው የጥልቅ ተሀድሶ ግምገማ  እንደተረጋገጠው ቀጣዩንና  ወሳኙን የህዳሴ   ጉዞ ጠባብነት፣ በሃይማኖት ሽፋን የሚራመድ የአክራሪነት አመለካካትና ተግባር፡ ሙስናና ብልሹ አሰራሮች፣ የውስጠ ድርጅት መዳከም የወለደው ፀረ- ዴሞክራሲ ፣  ለስልጣን ካለ የተዛባ አመለካካትና ተግባር የሚመነጩ የኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከቶችንና ተግባራትን የመታገል ጉዳይ      የሞት የሽረት  ትግል  የሚጠይቅ የወቅቱ አጀንዳ  ሆኗል፡፡

ድርጅታችን ደኢህዴን በሚቀጥሉት ጊዜያት     ክልላችን የልማታዊና ዴሞክራሲያዊ አስተሳሰብና ተግባር የበላይነት የያዘበት፣ ማህበራዊ ፍትህና ህብረ-ብሔራዊ አንድነታችን ወደ ላቀ ደረጃ የደረሰበት፣ የዳበረ መካከለኛ ገቢ ላይ የደረሰ ክልል ሆኖ የማየትን   ራዕይ አስቀምጧል   ፡፡ ይህንን ራዕይ እውን ማድረጊያ  ስትራቴጂያዊ የትግል አቅጣጫዎችንም ለይቷል፡፡ይህንን ራዕይ እውን ለማድረግ ጠንካራ  ልማታዊና ዴሞክራሲዊ ድርጅት የመገንባት   ተግባርን  ማሳካት የመጀመሪያው  ወሳኝ ጉዳይ  ተደርጎ ተቀምጧል፡፡የልማታዊና ዴሞክራሲያዊ ድርጅታችን የፖለቲካ ሥራ ግቡ በልማታዊና ዴሞክራሲያዊ አስተሳሰብ፣ አሠራርና አደረጃጀት ላይ ተመስርቶ  በተስተካከለ አመለካከት  የተገነባ ፣የዳበረ ክህሎት የፈጠረ፣ ንድፈ ሀሳባዊ ዕውቀቱ የጐለበተ፣ ለህዝብ ውግንና እና ለመደባዊ ትግል  ዝግጁነቱ እያደገ የሚሄድ ግንባርቀደም ኃይል መፍጠር ነው፡፡ስለዚሀም  በአመለካከቱ፤ በእውቀቱ፤ በክህሎቱና በስነ ምግባሩ የበቃና የድርጅቱን መርሆች የተላበሰ፣ እሴቶቹንም በሚገባ ጨብጦ የእለት ተዕለት የተግባር መመሪያው ያደረገ አመራርና አባል  የመፍጠር ጉዳይ እንደአገርም ሆነ እንደ ክልል ቁልፍ የአቅም ግንባታ አቅጣጫ ሆኖ ተቀምጧል፡፡

 

በአጠቃላይ ደርጅታችን  ሃያ አምስተኛውን  ዓመት የምስረታ በዓሉን መሰረት አድርጎ የሚከተለውን ጥሪ አስተላልፏል፡-

 

የተከበራችሁ መላው የደኢህዴን አባላትና ደጋፊዎች፡-

የደኢህዴን ያለፉት ሃያ አምስት ዓመታት የትግልና የድል ጉዞ ስናነሳ   የመላው ድርጅታችን አመራር፣ አባላትና ደጋፊዎች ብሎም የምልዓተ ህዝቡ እንቅስቃሴ ውጤቶችን ማስታወሳችን እንደሆነ ይታወቃል፡፡   ደኢህዴን የፕሮግራም ፣የዓላማ፣ የመርሆና  የተልዕኮ አንድነትና መደባዊ አሰላለፍ ያስተሳሰራቸው ታጋዮች  ስብስብ መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ የደኢህዴን አመራርና  አባላት አምሳለ -ደኢህዴን ሆነው የትግሉና የስኬቱ ሂደት ተዋናይ በመሆን ከፍተኛ ሚና ተጫውተዋል፡፡ ባለፉት ሃያ አምስት ዓመታት ውስጥ  ደኢህዴን ድርጅታዊ  አቅሙና ሚናው እያደገ ፣ አባልና ደጋፊውም  እየተጠናከረ በመምጣቱ በዴሞክራሲና  በልማት ግንባታው ረገድ ትላልቅ  ስኬቶችን  ማስመዝገብ ተችሏል፡፡ እየተመዘገበም ይገኛል፡፡

ደኢህዴን /ኢህአዴግ  የነደፋቸው የዕድገትና ብልጽግና ፖሊሲዎችና ማስፈጸሚያ ስልቶች   ውጤታማ እንዲሆኑ ተዋናይ ከመሆን አንፃር የአባላትና የደጋፊዎች ሚና የጎላ ነበር፡፡ በአጠቃላይ በዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታው፣ በፀረ ድህነትና ኋላቀርነት ትግሉ እንዲሁም መልካም አስተዳደርን በማስፈኑ  ሂደት፣  የህዝቡን የተደራጀ ንቅናቄ በመደገፍ፣ በማስተባበርና በማንቀሳቀስ በሃያ አምስቱ ዓመታት ለተመዘገቡት ድሎች የአመራራችን ፣  የአባላትና የደጋፊው   አስተዋጽኦ ከፍተኛ  በመሆኑ ደኢህዴን ለአባላቱና ለደጋፊዎቹ በዚህ አጋጣሚ ልፋታችሁ ደማቅ ድል አስመዝግቧል፤ እንኳን ደስ አላችሁ ይላል፡፡ ትግላችሁንም አጠናክራችሁ በመቀጠል ከፊት ለፊት የሚጠብቀንን አቀበት በህዝባዊ ወኔና  ጽናት ለመውጣት ዝግጁነታችሁን እንድታድሱ ጥሪውን ያቀርባል፡፡

በተለይ በጥልቅ ተሀድሷችን በየአካባቢዎቻችን የተለዩትን ብልሽቶች  ያለምህረት በመታገልና በማስወገድ  የድርጅታችንና የመስመሩን ህዝባዊነትና ሃያልነት ይበልጥ በማረጋገጥ የህዳሴ መዳረሻችን የለመለመና የተደላደለ እንዲሆን ንቅናቄያችንን አንድናቀጣጥል ደኢህዴን በአጽኖት  ይጠይቃል፡፡ የስርዓቱ አደጋ ብለን  ያሰመርንባቸው ጠባብነት፣ በሃይማኖት ሽፋን የሚራመድ አክራሪነት፣ ሙስናና ብልሹ አሰራሮች እንዲሁም ፀረ ዴሞክራሲ  የህዝቦችን የጋራ ጥቅሞች ከማደናቀፍ እንዲገቱና ከመሰረታቸውም እንዲወገዱ ትግላችንን እናጠናክር፡፡

ደኢህዴን የረጂም ጊዜ ራዕይ ሰንቆ  ግቡንም ለማሳካት አቅዶ የሚንቀሳቀስ ህዝባዊ ድርጅት በመሆኑ    የመጪውን ጊዜ  ታሳቢዎች ከግምት ውስጥ በማስገባት  የቀጣይ  ዓመታት  ራዕይና ግቦችን ቀይሷል፡፡  ይህ ራዕይና ግቡም    ያለአባለቱና ደጋፊዎቹ  ጠንካራ ትግል ሊሳካ እንደማይችል ለመላው አባላትና ደጋፊዎችም ግልጽ ነው፡፡ ስለሆነም ደኢህዴን ለወጠናቸው ህዝባዊ ራዕይዎችና ግቦች እውን መሆን መላው አባላትና ደጋፊዎች በትጋት እንዲረባረቡ ደኢህዴን ጥሪውን ያቀርባል፡፡  

 

 

ክልላችን አርሶአደሮችና  አርብቶአደሮች ፡-

የተከበራችሁ የክልላችን  አርሶ አደሮችና   አርብቶ አደሮች እንዲሁም በገጠር የምትገኙ  የክልሉ ህዝቦች በአጠቃላይ ፣ በደኢህዴን የሃያ አምስት ዓመታት ጉዞ ውስጥ ዋነኛ ማህበራዊ መሰረት ሆናችሁ  በመታገልና በማታገል  እጅግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክታችሁዋል፡፡ክልላችን ብሎም እንደሀገር የፈጣን ዕድገት ባለቤት እንድንሆን የማይተካ ድርሻችሁን እየተወጣችሁ ትገኛለችሁ ፡፡ አገራችን ለዘመናት ከምትታወቅበት ድህነትና ኋላቀርናት  ለመላቀቅ የተከፈተው ዘመቻ በትክክለኛ አቅጣጫ እየተጓዘ ይገኛል፡፡ ድህነት የሚሸነፍ ጠላት እንደሆነ ማስመስከር ጀምራችሁዋል፡፡ ለዚህ አስተዋጽኦዋችሁም   ደኢህዴን እንደወትሮው ሁሉ   ታላቅ ክብርና እውቅና ይሰጣል፡፡

ካለእናንተ የተደራጀና የነቃ ድጋፍ፣ ተሳትፎና ትግል ውጭ  የክልላችን ህዳሴ እንደማይረጋገጥ ድርጅታችን ጠንቅቆ ያውቃል፡፡  ለእያንዳንዱ ስኬት መረጋገጥ አርሶአደሩ፣ ከፊልአርብቶ አደሩና አርብቶአደሩ ወሳኝ   ሚና እንደሚጫወትም  ተገንዝቦ እያንቀሳቀሰና እውቅና እየሰጠ የመጣ ድርጅትም ነው ደኢህዴን ፡፡

ድህነትንና ኋላቀርነትን  ደግሞ   ከሀገራዊ ተጨባጭ ሁኔታ ጋር ተስማሚ የሆኑ  የኢኮኖሚ ፕሮግራሞችን፣ ፖሊሲዎችንና ስትራቴጂዎችን በመንደፍ ብቻ መርታት አይቻልም፡፡ ከሀገራዊና ክልላዊ ተጨባጭ ሁኔታው ጋር የተስማማ የፖለቲካ ፣የኢኮኖሚና የማህበራዊ ፕሮግራም   መነሻ ያደረጉ ፖሊሲዎችንና ስትራቴጂዎችን መንደፍ መቻል በራሱ የአንድ ፓርቲ ህዝባዊነትና የለውጥ ሀይልነት  መለኪያ ትልቁ መሳሪያ ቢሆንም ፖሊሲዎቹና ስትራቴጂዎቹ በተደራጀና በነቃ የህብረተሰብ ተሳትፎ ካልተደገፉ መምከናቸው አይቀሬ ነው፡፡  የመንግስታችንን ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች ወደ ተግባርና ውጤት በማሸጋገሩ እልህ አስጨራሽ ትግል ውስጥ   አርሶአደሮቻችን፣ ከፊልአርብቶ አደሮቻችንና አርብቶአደሮቻችን ሁነኛ ተዋነዮች ናችሁ፡፡ የክልላችን አርሶአደሮችና አርብቶአደሮች የደኢህዴን/ኢህአዴግ መንግስት ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች መሬት እንዲነኩና እንዲሳኩ የተጫወቱት ሚና  አስደናቂ ነው፡፡ ደኢህዴንም   የእነዚህ ብርቱ የለውጥ ሀይሎች መሪ በመሆኑ ታላቅ ኩራትና በራስ መተማመን ይሰማዋል፡፡

የደኢህዴንን  ምስረታ ሃያ አምስተኛውን ዓመት  በዓል ስናከብር ለቀጣዩ የትግልና የስኬት ጉዞ ተጨማሪ አቅምና ዝግጁነት በመላበስ፣ የለውጦቻችንን ፍጥነት ይበልጥ ከፍ ለማድረግ  የአስተሳሰብና የተግባር አንድነታችንን በማደስ በተደራጀ ሰራዊትነት ለመረባረብ   ዝግጁነትን በማረጋገጥ ሊሆን ይገባል ፡፡ የፀረ- ድህነትና ኋላቀርነት  ትግሉን ከፍ በማድረግ ድህነትንና ኋላቀርነትን በተቻለ መጠን በግለሰብ ፣በቤተሰብ፣በአካባቢና በክልል እንዲሁም  በሀገር ደረጃም ጭምር ለማስወገድ  ራሳችንን እየዘጋጀን ሊሆን ይገባል፡፡  ከዚህ አኳያ ምርታማነትን በማሳደግ ዙሪያ የሚታዩ ማነቆዎችን ለማስወገድ ከወዲሁ መዘጋጀት ይጠበቅብናል፡፡የግብርናና ገጠር ልማት ስራችንን በማዘመን የገጠር ትራንስፎርሜሽንን ማረጋገጥ ከፍተኛ  ቁርጠኝነት እንደሚጠይቀን ተገንዝበን ትግሉን ማጠናከር ይገባናል፡፡

የተከበራችሁ  የክልላችን መምህራንና   ፐብሊክ ሰርቫንቶች ፡--

በልማታዊ ዴሞክራሲያዊ ድርጅታችን የሃያ አምስት ዓመታት ጉዞ ውስጥ የክልላችን መምህራንና  ፐብሊክ ሰርቫንቶች  የጉላ ስፍራ አላቸው፡፡  ትምህርትን ለዜጎች  ለማደረስ በተደረገው ርብርብና በተገኘውም  ውጤት ውስጥ መምህራን የአንበሳውን  ድርሻ ይይዛሉ፡፡ የሰው ልጆችን የመቅረጽ ታላቅ ሙያዊ ሀላፊነት የተሸከመው መምህር  በክልላችንም ይሁን በሀገራችን ለተረጋገጠው የትምህርት ልማት ስኬት ያበረከተው አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው ፡፡ ተጠናክሮም መቀጠል ይኖርበታል፡፡ መምህርነት ቅድመ ሁኔታ የማይገድበው ወላጅነትና ባለአደራነት በመሆኑ ትምህርትን ለዜጎች ከማዳረሱ ጥረት ጎን ለጎን ለጥራቱም በተሟላ ደረጃ መረጋገጥ የመምህሩ ሚና ከፍተኛ ነው፡፡ ስለሆነም  ወቅቱ በሁሉአቀፍ ስብዕናው የተገነባ ዜጋን ማፍራትና  ተወዳዳሪነትንም ማረጋጋጥ  ጠይቋልና  ይህን  ተልዕኳአችሁን  ለመወጣት ይበልጥ አንድትጠናከሩ ድርጅታችን ክልላዊ ጥሪ ያቀርባል፡፡

     በደኢህዴን/ኢህአዴግ የሚመራው ልማታዊ ዴሞክራሲያዊ መንግስት የነደፋቸውን ፖሊሲዎች እና  ከፖሊሲው የሚመነዘሩ    ዕቅዶችን ከማስፈጸምና መፈፅም አንፃር ፐብሊክ ሰርቫንቱ ያደረጋቸው ርብርቦች የሚደነቁ ናቸው፡፡ የክልሉ ህዝብ እስከ 80 በመቶ ድረስ በሚገኝበትና የአጠቃላይ ኢኮኖሚው  ዋና መሠረት በሆነው በገጠርና በግብርናው መስክ አስደናቂ ውጤት እንዲመዘገብ  ፐብሊክ ሰርቫንቱ በተለይም የግብርና ሙያተኛው ለአርሶ አደሩና አርብቶ አደሩ ያበረከተው አስተዋትኦ የማይተካ ሚና ነበረው፡፡ በትምህርት ፣ በጤና፣ በመሰረተ ልማትና በከተማ ልማት መስኮች  ለተቀዳጀናቸው ድሎችም የፐብሊክ ሰርቫንቱ አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑን በመገንዘብ ደኢህዴን ምስጋናውን ያቀርባል፡፡ ይህ አበረታች የፐብሊክ ሳርቫንቱ  እንቅስቃሴም  ተጠናክሮ እንዲቀጥል ያሳስባል፡፡

በተለይም በቀጣይ ይበልጥ መታረም  እንዳለባቸው በጥልቅ ተሀድሷችን የለየናቸው ጉድለቶችን ማረም ጊዜ የሚሰጠው አይደለም ፡፡ ይኸውም  የኪራይ ሰብሳቢነት ምንጮችን ከማድረቅና በአገልግሎት አሰጣጡ ላይ የሚታዩትን ጉድለቶች ለማረም  ፐብሊክ ሰርቫንቱ የጀመራቸው ጥረቶች ይበልጥ እንዲጠናከሩ ደኢህዴን ጥሪውን ያቀርባል፡፡  ለልማታዊ የፖለቲካ ኢኮኖሚው የበላይነት  መረጋገጥ ፐብሊክ ሰርቫንቱ የበኩሉን ማበርከት ፤  በተሠማራበት መስክም  ውጤታማነቱን ለማሳደግና የስርዓቱ ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ መርሆዎችም በተሟላ ሁኔታ ተግባር ላይ እንዲውሉ በማድረግ ሂደት የህዝቡን እርካታ እያረጋግጥን መሄድ አለብን፡፡

  የተከበራችሁ የክልላችን ሴቶችና ወጣቶች ፡-

የሴቶችንና የወጣቶችን ሁለንተናዊ ተሳትፎና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ ከመቼው ጊዜ በላቀ ዝግጁነት ላይ ሆኖ ደኢህዴን ሃያ አምስተኛውን የምስረታ በዓሉን እያከበረ ይገኛል፡፡   በእስከአሁኑ እንቅስቃሴ በገጠርና በከተማ የተጎናፀፍናቸውን ስኬቶች በመጠበቅና በማስፋት መላው ሴቶችና ወጣቶች ለፍትሃዊ ተጠቃሚነታቸው መረጋገጥ  እንዲተጉ ድርጅታችን  ያመናል፡፡   የክልላችን ሴቶችና ወጣቶችም ከደኢህዴን ጎን በመሆን ጠንካራና የተደራጀ ተሳትፎ በማድረግ ለሁሉአቀፍ ተጠቃሚነታቸው መረጋገጥ  እንዲረባረቡ ደኢህዴን ጥሪውን ያስተላልፋል፡፡   ለመላው ሴቶችና ወጣቶች ፍትሃዊ ተጠቃሚነት መረጋገጥ የድርጅትና የመንግስት መዋቅሩ እንዲሁም መላው ሴቶችና ወጣቶችም ትግላቸውን እንዲያጠናክሩም በአጽንኦት ያሳስባል፡፡

 

ለጥቃቅንና አነስተኛ አንቀሳቃሾችና ልማታዊ ባለሀብቶች ፡-

በጥቃቅን፣በአነስተኛና መካከለኛው የኢንዱስትሪ ዘርፍ አንቀሳቃሽነት የተሠማራው ሀይል የክልሉንና የሀገሪቱን የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ሽግግር ከማሳካት አንፃር ተልዕኮው ከፍተኛ ነው፡፡ በእስከ አሁኑ እንቅስቃሴም የየዘርፉ አንቀሳቃሾች ጅምር እንቅስቀሴ እየጎለበተ መሄድ ይጠበቅበታል፡፡   በተለይም ቴክኖሎጂን በመቅዳት ፣ በማላመድ፣የውጭ ምንዛሪን የሚጠይቁ  ማቴሪያሎችን በማምረትና  ፈጠራን በማሳደግ ረገድ የተለየ ትኩረት ሰጥተን ርብርብ ማድረግ አለብን፡፡ ዘርፉ የሥራ ዕድልን ከመፍጠርና  ገቢም  ማስገኛ ከመሆኑ ባሻገር ለኢኮኖሚው መዋቅራዊ ሽግግር ወሳኝ በመሆኑ ተጠናክሮ መቀጠል ይገባዋል፡፡  በአምራቹ ዘርፍ በጠንካራ ራዕይና ቆራጥነት ተሰማርቶ  ከልምድ እየተማሩ   የኢንዱስትሪ ልማቱን  ከማጠናከር አንፃር የሚታዩትን ውስንነቶች በመሻገር ዘርፉን ወደታለመለት ግብ የማድረስ ጉዳይ እጅግ አንገብጋቢ  ነው፡፡ የደኢህዴን የቀጣይ ዓመታት ራዕይና የትኩረት አቅጣጫም የኢንዱስትሪ ግንባታውን ደረጃ በደረጃ ማሳደግ  በመሆኑ ለዚህ ራዕይ  እውን መሆን ጠንካራ መደላድል መገንባት ከኢንተርፕራይዞቻችን ይጠበቃል፡፡

ልማታዊ ባለሀብቱ በኢኮኖሚ ዕድገቱ ውስጥ ዘርፈ ብዙ ሀላፊነቶችን  የተሸከመ ነው፡፡ በአንድ በኩል በልማታዊ መንገድ ተንቀሳቅሶ ሀገር በቀል ኢንዱስትሪዎችን በመገንባትና በማስፋፋት የሥራ ዕድል ፈጠራንና   የቴክኖሎጂ ሽግግር ተግባራትን ማፋጠን ይጠበቅበታል፡፡  በሌላ በኩል ደግሞ እሴቶችን ጨምሮ የማምረቱን ባህል በማዳበር ከግብርናው ወደ ኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚ  ሽግግሩን  ለማፋጠን ሚናውን ማበርከት ይጠበቅበታል፡፡ ስለሆነም ስርዓቱ የፈጠረለትን ምቹ ሁኔታ በልማታዊ መንገድ ተጠቅሞ የራሱንም የሀገሪቱንም እድገት ለማፋጠን ርብርቡን ማጠናከር አለበት፡፡ ልማታዊ ባለሀብቱ በተለይም በአምራቹ ዘርፍ ከመሰማራት አንጻር የሚታየውን ድክመት በማረም ለረጂሙ ጉዞ በአጭሩ ታጥቆ እንዲነሳ ደኢህዴን ጥሪውን ያስተላልፋል፡፡

እንደዚሁም የንግዱ ማህበረሰብ በአጠቃላይ እና የከተማ ነዋሪው በልማትና በመልካም አስተደዳር ግንባታው ሂደት የተጀመረውን እንቅስቃሴ በማጎልበት፣  የድህነትን ዕድሜ  የማራዘምና የጋራ ተጠቃሚነትን የማቀጨጨ ሚና ያለውን የኪራይ ሰብሳቢነትን አመለካከትና ተግባር  በመዋጋት  በኩል ትግሉን ሊያጠናክር ይገባል፡፡

ከክልሉ ውጭ በአዲስ አበባና በሌሎችም የአገሪቱ ክፍሎች የምትገኙ አባሎቻችንና ደጋፊዎቻችን አገራዊ ህዳሴው እንዲረጋገጥ በያላችሁበት አካባቢና  በተሰማራችሁበት የተግባር መስክ አተዋጽኦችሁን ማበርከት ይጠበቅባችሁዋል፡፡ አንድ  የጋራ አገራዊ  የኢኮኖሚና የፖለቲካ   ማህበረሰብ በመገንባቱ ሂደት ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ ሚናችሁ የበለጠ ተጠናክሮ እንዲቀጥል  ማድረግ ይጠበቅባችሁዋል፡፡

ከሀገር ውጭ በተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች የምትገኙ አባሎቻችንና ደጋፊዎቻችን ክልላዊና አገራዊ ገጽታን የመገንባቱን እንቅስቃሴ ይበልጥ የማጠናከር፣ በተለይም ደግሞ  የአንዳንድ  ጽንፈኛ ሀይሎች የተሳሳተ  አመለካካትና ተግባር  የኢትዮዽያ ህዝቦችን የጋራ ጥቅሞችና አብሮነት የሚጎዳ መሆኑን የማስጨበጥና   የማስተካከል ተልዕኮአችሁን ማጎልበትም ይጠበቅባችሁዋል፡፡ በእውቀታችሁ፣ በሀብታችሁና በሙያችሁ አገራችሁን ብሎም ክልሉን  የመደጋፉን ተግባር  እንድታጠናክሩም ደኢህዴን ጥሪ ያቀርብላችሁዋል፡፡

ደኢህዴን ከእህት እና  አጋር ድርጅቶች  ጋር እጅ ለእጅ ተያይዞ  የተጓዘባቸው ያለፉት የስኬት ዓመታት ልምዶችና መደጋገፎች ለቀጣዩ  የትግልና የድል ጉዞ  ምቹ መሰረት ሆነው የሚያገለግሉ ናቸው ፡፡ ለእሰከአሁኑ የድርጅታችን  የትግልና የድል ጉዞ  ስኬታማነት  የእህትና የአጋር ድርጅቶች ላበረከቱት  አሰተዋጽኦ ደኢህዴን አድናቆቱን ይገልጻል፡፡    አንድ ጠንካራ አገራዊ    የጋራ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ማህበረሰብ የመገንባቱ ሂደት  መደጋጋፍን፣ መረዳዳትንና ለጋራ ግብ አብሮ መዝመትን የሚጠይቅ መሆኑ አያጠያይቅም፡፡ ስለሆነም ትብብሩና መደጋገፉ እንደወትሮው ሁሉ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ደኢህዴን ዝግጁነቱን በዚህ አጋጣሚ ያረጋግጣል፡፡

በአጠቃላይ ባለፉት  አምስት የምርጫ ዙሮችና  ሂደቶችም የክልሉ ብሄሮች፣ ብሔረሰቦችና  ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ መብታቸውን ተጠቅመው፣ ወደውና ፈቅደው  ይሁንታቸውን ስለሰጡት  ታላቅ ምስጋናውን ደኢህዴን እያቀረበ ፣ድምፆቻቸውንና አደራቸውን በታላቅ አክብሮትና ትጋት ለመወጣትም  ቃሉን በዚህ አጋጣሚ ያድሳል፡፡

 መጪው ጊዜ ከደኢህዴን / ኢህአዴግ ጋር የህዳሴና በተስፋ የተሞላ እንደሚሆን ድርጅታችን ደኢህዴን ጥርጥር የለውም፡፡  መላው የክልሉ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች የጀመሩት በስኬት የተጀበ ጉዞ ወደ ህዳሴው ማማ እንዲዘልቅ  ደኢህዴን ወቅቱ የጠየቀውን የመሪነት ቁመና አሟልቶ በመገኘት   እናንተን ለማገልገል ዝግጁ መሆኑን ያረጋግጣል፡፡     ወደ ህዳሴው ማማ  ፈጥናን ለመዝለቅ የክልሉ ብሄሮች፣ብሄረሰቦችና ህዝቦች እንደዲሁም መላው የሀገራችን ህዝቦች   ከመቼውም ጊዜ የላቀ የጋራ አቋምና  መግባባት ገንብተው የሰላም፣ የዴሞክራሲና የልማት ግንባታውን   ለማፋጣን    ከደኢህዴን/ኢህአዴግ  ጎን እንዲቆሙ  ድርጅታችን  ጥሪውን  በታላቅ አክብሮት ያቀርባል፡፡

 

ድልና ድምቀት  ለደኢህዴን 25ተኛ ዓመት የምሰረታ በዓል

ክብርና ሞገስ ለትግሉ ሰማዕታት!

 

ምንም ዓይነት ተጨማሪ ይዘቶች አልተገኘም!