ሊግ

የደቡብ ክልል ሴቶችና ህጻናት ጉዳይ ቢሮ ዓመታዊ የሴክተር ጉባኤ በአርባምንጭ ከተማ

የደቡብ ክልል ሴቶችና ህጻናት ጉዳይ ቢሮ ዓመታዊ የሴክተር ጉባኤ በአርባምንጭ ከተማ ተጀመረ ፡፡


በጉባኤው ላይ ቀዳማዊት እመቤት ሮማን ተስፋዬ እና የኢፌድሪ የሴቶችና ህጻናት ሚኒስቴር ሚኒስትር ወ/ሮ ደሚቱ አምቢሳን ጨምሮ በርካታ የክልልና ዞን ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች እንዲሁም የሴቶች አደረጃጀቶች አባላት ተገኝተዋል፡፡
የክልሉ የሴቶችና ህጻናት ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ሂክማ ከይረዲን ጉባኤው ስኬቶች የሚዘከሩበት ፣ ድክመቶች የሚታረሙበት ፣ ትርጉም ያላቸው የልማት ተሞክሮዎች የሚሰፉበት ፣ ቅንጅታዊ አሰራር የሚጠናከርበት እና ለቀጣይ የሴክተሩ ስራዎች የተሻለ አፈጻጸም የሚረዱ ሃሳቦች የሚገኙበት እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
በጉባኤው የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የኢፌድሪ የሴቶችና ህጻናት ሚኒስቴር ሚኒስትር ወ/ሮ ደሚቱ አምቢሳ እንደገለጹት በክልሉ በተደራጀ የሴት የልማት ቡድኖችና በእማዎራዎች ላይ የታዩ አመርቂ ስራዎች የሴቶች የልማት ፓኬጅና ስትራቴጂውን ተግባራዊ ማድረግ የቻሉ መሆናቸውን የሚያሳይ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ከዘርፉ ተሻጋሪነት ባህሪ አንጻር የሚነሱ ማናቸውንም ጥያቄዎች በሚያጠግብ መልኩ ለመመለስ በቅንጅት መስራትና በሁሉም አካላት ዘርፈ ብዙ ምላሽ መስጠት ስትራቴጂያዊ አማራጭ በመሆኑ የተጓዝንበትን የዘርፉን የልማት ጎዳና በትኩረት መገምገምና ልማታዊ አቅጣጫን ለይቶ በጋራ መንቀሳቀስ ያስፈልጋልም ብለዋል ፡፡
ቀዳማዊት እመቤት ሮማን ተስፋዬ በበኩላቸው ሴቶች ወደ አደባባይ ወጥተው በኢኮኖሚም ሆነ በሌሎች አመራር ሰጪነት አቅማቸው ሲጎለብት የቤታቸውን ኃላፊነት ጥለው ባለመሆኑ ሊኖርባቸው የሚችለውን ድርብ ጫና ለመጋራት የወንዶች ከፍተኛ እገዛ እንደሚያስፈልጋቸው ገልጸዋል፡፡
የሴቶችን ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ መብቶች የማረጋገጥ ጉዳይ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት ሊሰራ እንደሚገባም አመልክተዋል፡፡
የሴቶችን የኢኮኖሚያዊ አቅም ለመገንባት ሲባል አካላዊ ብቃታቸውን መጠበቅ ስለሚያስፈልግ ሴቶችን በቀላሉ ሊያጠቁ የሚችሉ በሽታዎችን የመከላከሉ ስራ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ቀዳማዊት እመቤት ሮማን ተስፋዬ አሳስበዋል፡፡
ሐምሌ 29/2009 /የደቡብ ክልል የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት/

ምንም ዓይነት ተዛማጅ መረጃ አልተገኘም!