ኮሚቴ

በስኬት የታጀበው ጉዟችን፣ ወደ ህዳሴው ማማ !

በዓሉን ስናከብር፣ ወደ ህዳሴው ማማ የሚያዘልቀንን መደላድል እያጠናከርን ሊሆን ይገባል!!

" በስኬት የታጀበው ጉዟችን፣ ወደ ህዳሴው ማማ ! " በሚል መሪ ቃል የደኢህዴን ምስረታን 25ተኛ ዓመት በዓል በማክበር ላይ እንገኛለን። በዓሉ ከቀበሌ ጀምሮ በየደረጃው በተለያዩ ዝግጅቶች በመከበር ላይ ነው። በዓሉን ስናከብር የእሰከአሁኑን የትግልና የስኬት ጉዞ እየገመገምን፣ ስኬቶቹን ለማስጠበቅ ቃል እየገባን፣ ያጋጠሙንን ፈተናዎች ገጽታ ደግሞ እየፈተሽን፣ እነዚህን ፈተናዎችም በወሳኝ ደረጃ ማምከን የሚያስችለንን አቅምና ዝግጁነት በመገንባት መሆን አለበት።

የራዕያችን ማእከል የፀረ- ድህነትና ኋላቀርነት ትግሉን በማቀጣጠል ወደ ዳበረ ገቢና ኑሮ ደረጃ መሸጋገር ነው። በራዕያችን ላይ በየደረጃው የምንፈጥረው ግልጽነትና መግባባት ፋይዳው እጅግ ከፍተኛ ነው። ድርጅታችን ከረጂም ጊዜ አንጻር ክልሉና ህዝቡ ሊደርሱበት የሚገባውን ራዕይ የሚያስቀምጥበት መሰረታዊ ምክንያት መሪው ድርጅት ብቻ ሳይሆን መላው ህዝብም ጭምር የነገውን ተስፋና እድል ከወዲሁ ጨብጠው ለተፈጻሚነቱ ሁሉም የየበኩሉን ከፍተኛ ሚና እንዲጫወት ለማነሳሳት ነው።

ሀገራችን የምትመራው በመድብለ ፓርቲ ስርዓት መሆኑ ይታወቃል። ስልጣን በህዝብ ምርጫ የሚገኝ ህዝብን ማገልገያ መሳሪያ መሆኑ ላይም የጋራ መግባባት የመፍጠሩ ሂደት እያደገ መጥቷል። ደኢህዴንም የቀጣይ 25 ዓመታት ራዕይና ስትራቴጂያዊ አቅጣጫዎችን ሲያስቀምጥ የመደብለ ፓርቲ ስርዓቱን ለማጠናከር እንደ ገዢ ፓርቲ ለዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታው የሚጠበቅበትን ሁሉ ለማበርከት ዝግጁነቱን እያረጋገጠ ነው።
ደኢህዴን /ኢህአዴግ በራዕይ የሚመራ ድርጅት ነው። ስለሆነም ከየት ወደየት እንደሚጓዝ ግልጽ ፍኖተ ካርታ ማስቀመጥ ይጠበቅበታል። የድርጅቱ ራዕይ የእያንዳንዱን ዜጋ ሕይወት በእያንዳንዱ ዜጋ ልማታዊና ፍትሃዊ ተሳትፎና ጥረት የሚሻሻልበትን መንገድ አመልካች ነው። ስለሆነም የድርጅቱ ራዕይ የመላው ህዝብ ወይንም የአብዛኛው ህዝብ ራዕይ እንዲሆን ተከታታይነት ያለው የጋራ መግባባት የመፍጠር ተግባር በየደረጃው ሊከናወን ይገባዋል።

!በዓሉ የጀመርነውን የህዳሴ ጉዞ ለማፋጠን የራሱን አስተዋጽኦ እንዲያበረክት ይጠበቃል። " በስኬት የታጀበው ጉዟችን፣ ወደ ህዳሴው ማማ ! " የሚለው መሪ ቃልም የማሽቆልቆል ጉዞውን ከመግታት ባሻገር ስኬቶቻችንን ነቅተን በመጠበቅ፣ በአዳዲስ ስኬቶች ታጅበን ወደ ህዳሴው ማማ እንወጣለን የሚል መልእክትን ያዘለ ነው። ወደ ህዳሴው ማማ የመዝለቁ ጉዞም አልህ አስጨራሽና ከባድ መሆኑን ታሳቢ በማድረግ ለወሳኙ ትግል ራሳችንን ማዘጋጀት ይጠበቅብናል። በተለይም መላው አባሎቻችንና ደጋፊዎቻችን የበዓሉን መሰረታዊ ፋይዳ በአግባቡ በመጨበጥ ትግሉን የማስፋት ሀላፊነት ተጥሎባቸዋል።

ደኢህዴን አብዮታዊ ዴሞክራሲ ጋዜጣ ዕትም 243 ርዕሰ አንቀፅ

ምንም ዓይነት ተዛማጅ መረጃ አልተገኘም!